ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ከጥቂት ቀናት ወዲህ ወታደራዊ እንቅስቃሴ እየታየበት ባለው ኢትዮጵያን ከሱዳን ጋር በሚያዋስነው የድንበር አካባቢ በነዋሪዎች ጉዳት መድረሱ ተሰማ።
የምዕራብ ጎንደር ዞን አስተዳዳሪ አቶ ደሳለኝ ጣሰው በግጭቱ አራት ሰዎች ላይ ጉዳት ደርሶ ሁለቱ መሞታቸውን እና ከ1 ሺኅ 700 በላይ ሰዎች ከድንበሩ አካባቢ መፈናቀላቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል። ጥቃቱን ተከትሎ እስከ 200 የሚጠጉ አርሶ አደሮች ለዘመናት ያፈሩት ከፍተኛ ግምት ያለው ንብረት በሱዳን ወታደሮች መውደሙንም በተያያዥነት አስረድተዋል።
የሱዳኑ የማስታወቂያ ሚንስትር የሀገራቸው ወታደሮች በሁለቱ አገራት አዋሳኝ የድንበር አካባቢ በኢትዮጵያውያን አርሶ አደሮች ተይዞ የቆየ ካሉት መሬት ውስጥ አብዛኛውን መቆጣጠራቸውን መናገራቸውን ደግሞ ሮይተርስ ዘግቧል።
የሱዳን ሠራዊት በድንበር አካባቢ ባሉ ቦታዎች ላይ ጥቃት መሰንዘር የጀመሩት ከጥቅምት ወር ማብቂያ ጀምሮ ነበር ያሉት የምዕራብ ጎንደር ዞን አስተዳዳሪ፤ “ምንም እንኳን የሱዳኖች እንቅስቃሴ ጥቅምት 27 ጀምሮ የንብረት ጉዳትን ቢያደርስም በሰው ላይ ጉዳት ስላላደረሰ ነገሮችን ሳናሰፋና ሳናጋንን ለመያዝ ሞክረን ነበር” ብለዋል።