ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ለጃዋር መሀመድ አራት ሲም ካርዶችን ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ሊያቀብል ሲል ተይዟል የተባለ ተጠርጣሪ ፍርድ ቤት ቀረበ።
ሃምዛ ጀማል መሃመድ ይባላል የተሰኘው ግለሰብ ታህሳስ 9 ቀን 2013 ዓ.ም አንደኛውን ሲም ካርድ በኦ ኤም ኤን ድርጅት ስም ማውጣቱን የገለጸው የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምርመራ ዘርፍ፤ ሦስቱ ሲም ካርዶች ደግሞ በግለሰብ ስም የወጡ መሆናቸውን ከኢትዮ ቴሌኮም አጣርቻለሁ ብሏል።
ተጠርጣሪው እነዚህን ሲም ካርዶች በመያዝ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት በመሄድ ጃዋር መሃመድን ልጠይቅ ነው በሚል ከገባ በኋላ ሲም ካርዶቹን ለጃዋር መሀመድ ሊያቀብል ሲል መያዙ ተረጋግጧል።
ተጠርጣሪው የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ቀርቦ ጉዳዩ እየታየ ሲሆን በቀጣይ ቀናት ውሳኔ ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል።