ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በሥድሥተኛው ሀገር ዐቀፍ ምርጫ ለመሳተፍ የፖሊሲ ሰነዶችን ማዘጋጀታቸውን አራት የፖለቲካ ፓርቲዎች አስታወቁ።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማሀበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ቀደም ሲል ምርጫ ከመራዘሙም አስቀድሞ ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሶ፤ ፓርቲው አዲስ እንደመመስረቱ ለምርጫው ውድድር የሚሆኑ 45 የፖሊሲ አማራጮችን ማዘጋጀቱን ገልጿል።
የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የሕዝብ ግንኙነት ሓላፊ ቀጀላ መርዳሳ ፓርቲያቸው ምንም እንኳን የውስጥ ችግር ቢኖርበትም በግንቦት ወር ለሚካሄደው ሀገራዊ ምርጫ ለመሳተፍ የቅድመ ዝግጅት ሥራ ተካሂዷል ብለዋል።
የብልፅግና ፓርቲ የምርጫ ዘርፍ ሓላፊ አቶ ዛዲግ አብርሃ ብልጽግና ለሥድሥተኛው ሀገራዊ ምርጫ ልዩ ትርጉም የሚሰጠው መሆኑን ጠቁመው፤ ፓርቲው ከቅርፅ ባለፈ የይዘትና የፕሮግራም ለውጥ አድርጎ በምርጫው እንደሚሳተፍም አረጋግጠዋል።
የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) የፖሊሲና ስትራቴጂ ጉዳዮች ሓላፊ አዲስ ሀረገወይን በበኩላቸው ምርጫውን ለማከናወን ቀደም ብሎ ፓርቲው ዝግጅቱን ሲያደርግ እንደቆየና ለዚህም ሲባል 25 የፖሊሲ ሰነዶችን ፓርቲው ማዘጋጀቱን ጠቁመዋል።