ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በትግራይ ክልል በሚገኘው የህወሓት ጽንፈኛ ቡድን ላይ በፌደራል መንግሥት እየተወሰደ ያለውን ሕግ ማስከበር ዘመቻ ተከትሎ በቁጥጥር ስር የዋሉና ተገደሉ ወታደራዊ መኮንኖችን ስም ዝርዝርን የአገር መከላከያ ሠራዊት ይፋ አደረገ።
የመከላከያ ሠራዊት ስምሪት መምሪያ ሓላፊ ብርጋዴል ጀነራል ተስፋዬ አያሌው፤ የመከላከያ ሠራዊትና የፌዴራል ፓሊስ በጋራ በወሰዱት እርምጃ መኮንኖቹ እንደተያዙና እርምጃ እንደተወሰደባቸው ጠቁመው፤ በርካታ ከህወሓት አመራሮች ጋር የተሰለፉ ወታደራዊ መኮንኖች እና የልዩ ኃይል አባላትም እጃቸውን እንደሰጡና እጅ ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆኑት እንተደመሰሱ ይፋ አድርገዋል።
ጥቅምት 30/2013 በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ ከ600 በላይ ሰዎች ተገድለውበታል የተባለውን የማይካድራውን ጭፍጨፋ መርተዋል የተባሉትን ኮሎኔል የማነ ገብረሚካኤልን ጨምሮ፤ ኮሎኔል ዓለም ገብረመድኅን፣ ኮሎኔል ቢንያም ገብረመድኅን፣ ኮሎኔል አምባዬ፣ ኮሎኔል ማዕሾ፣ ኮሎኔል ይርጋ ስዩም፣ ኮሎኔል ሃዱሽ፣ ኮሎኔል አጽብሃ፣ ኮሎኔል ተስፋዬ ገብረመድኅን፣ ኮሎኔል ዮሐንስ ካልአዩ፣ ኮሎኔል ተክለእግዚአብሄርና ሌተናል ኮሎኔል ብርሃኔ ቶላ መገደላቸው ተሰምቷል።
ከእነዚህ የጦር መኮንኖች በተጨማሪ በስም ያልተገለጹ አራት ኮሎኔሎች እንዲሁም ሁለት የዞን አመራሮች ተገድለዋል ያሉት ጀነራሉ፤ ተደብቀው እየተፈለጉ ያሉ የህወሓት ከፍተኛ አመራሮችና አባላትን መከላከያ ሠራዊትና ፖሊስ እየተከታተሏቸው መሆኑን እና ለዚህም የተለያዩ አካባቢዎችን ላይ ፍተሻና አሰሳ እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።