ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በምዕራብ ኦሮሚያ የምሥራቅ ወለጋ ዞን ዋና ከተማ ነቀምቴ፤ በአንዲት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ይደረጋል በተባለ የጸሎት ሥነ ሥርዓት ላይ ለመሳተፍ በተገኙ ምዕመናን መካከል በተፈጠረ መረጋገጥ አንድ ሰው መሞቱ ተሰማ።
” በእግዚአብሔር ምህረት ዓለም ዐቀፍ ቤተክርስቲያን ” ትናንት ሊካሄድ በታሰበ መንፈሳዊ ፕሮግራም ጋር በተያያዘ ከአርብ ሌሊት ጀምሮ በመግቢያ በሩ ላይ ተሰልፈው ለመግባት ሲጠባበቁ በነበሩ ሰዎች መካከል በተፈጠረ መገፋፋትና መረጋገጥ ጉዳት መድረሱን ተከትሎ አንዲት ሴት ወዲያውኑ ሕይወታቸው ሲያልፍ ስምንት ሰዎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል ነው የተባለው።
በተጠቀሰው ቤተክርስቲያን ይካሄዳል በተባለው የጸሎት ሥነ ሥርዓት ላይ ለመሳተፍ ከተለያዩ ቦታዎች በመምጣት ሲጠባበቁ የነበሩት ሰልፈኞች አርብ ሌሊት ወደውስጥ ለመግባት ያደረጉትን ግፊያ ተከትሎ በተፈጠረው መተራመስ ላይ ፖሊስ “ነገሩን አበርዳለሁ” በሚል ጥይት መተኮሱ ደግሞ አንዱ በሌላው ላይ እየተረማመደ መሸሹ አደጋውን በእጅጉ ሊያባብሰው ችሏል።