ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የህወሓት ነባር ታጋይ የነበረው የጀነራል ኃየሎም አርአያ ባለቤት የሆነችው አልጋነሽ በመቀሌ ከተማ ያሳፈነው እና በመጨረሻም ወደ ገደል ተወርውራ እንድትገደል ያዘዘው ስብሓት ነጋ መሆኑ ተሰማ።
ግለሰቧ ባለቤቷን ከገደሉት የህወሓት ጁንታ አባላት ጋር እንዴትና በምን ምክንያት ገጠመች? የሚለው ጉዳይ ሰሞኑን አነጋጋሪ ሆኖ ሰንብቷል።
የስብሐት ነጋን መያዝ ያበሰረው መከላከያ ሠራዊቱ በወቅቱ የኃየሎም አርአያ ባለቤት ከአሜሪካ እንደመጣች እና ልታመልጥ ስትል ገደል ገብታ እንደሞተች ገልጾ ነበር። ይሁን እንጂ መከላከያ ግለሰቧ ጦርነቱና ከበባው በአየለበት ሰዐት ለማምለጥ ስትሞክር ገደል መግባቷን ከነበሩ ምስክሮች መስማቱን እንጂ የሠራዊቱ አባላት በዐይናቸው አለመመልከታቸውን አረጋግጠዋል።
የህወሓት ገመናን በማጋለጥ የሚታወቀው ጋዜጠኛ አርአያ ተስፋማርያም ዛሬ በፌስ ቡክ ገጹ ይፋ እንዳደረገው የኃየሎም ሚስት ከአሜሪካ መቀለ ከተማ መግባቷን የሰማው ስብሐት ነጋ በታጣቂዎች እንድትታፈን አድርጎ እንደወሰዳት እና ተደብቆበት በነበረው ሰርጥ ውስጥ በስተመጨረሻ ላይ ለአጃቢዎቹ ገደል ውስጥ እንዲወረውሯት ማድረጉን አረጋግጫለሁ ብሏል።
ቀደምት የህወሓት ታጋይ የነበረው እና በአሁኑ ወቅት በአዲስ መልክ በተዋቀረው የትግራይ መስተዳድር ውስጥ በሓላፊነት የተሾመው አቶ ሊላይም ስለሁኔታው ሲያስረዳ “አልጋነሽን ከሥድሥት ወር በፊት በስልክ አውርቻታለሁ፣ እኔ እስከማውቀው ድረስ ለህወሓቶች ከፍተኛ ጥላቻ ነው ያላት። ከእነ ስብሐት ጋር የምትሆንበት ምንም ምክንያት የለም” በማለት ተናግሯል።