ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ሱዳን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እንደሚጠቅማት ብታውቅም፣ ከግብፅ ጋር በፈጠረችው ጊዜያዊ ፖለቲካዊ ጥምረት ምክንያት ከወዳጅ አገር የማይጠበቅ ተግባር በኢትዮጵያ ላይ እየፈፀመች መሆኑ ተነገረ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የውኃ ምህንድስና መምህር ዶክተር ይልማ ስለሺ ፤ ሱዳን የህዳሴውን ግድብ ጎርፍ በመከላከላከል እና ኤሌክትሪክ ኃይል በአነስተኛ ዋጋ እንድታገኝ በማድረግ ረገድ እንደሚጠቅማት ብታውቅም፣ ከግብፅ ጋር በፈጠረችው ፖለቲካዊ ትብብር ምክንያት በድርድሩ እና በድንበር አካባቢ ከወዳጅ ሀገር የማይጠበቅ ተግባር እየፈፀመች ነው ብለዋል።
ሱዳን በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ በሚደረገው ድርድርም ሆነ በኢትዮ-ሱዳን ድንበር አካባቢ እየሠራች ያለችው ሥራ ከወዳጅ ሀገር የሚጠበቅ አለመሆኑን ያመላከቱት ዶክተር ይልማ፤ በግድቡ ድርድር ላይ ሱዳንና ግብፅ የሚያሳዩት ተለዋዋጭ ባህሪ በአጋጣሚ ሳይሆን በፈጠሩት ፖለቲካዊ ትብብር መሆኑንም ጠቁመዋል።
ሁለቱም ሀገራት በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ በሚደረገውን ድርድር ሰበብ አድርገው በአባይ ወንዝ የውሃ ድርሻቸውን ለማስጠበቅ ፍላጎት እንዳላቸው ያስረዱት ባለሙያ፤ በተለይ ሱዳን የህዳሴው ግድብ ከጎርፍ አደጋ እንደሚታደጋት እና ኤሌክትሪክ ኃይል በርካሽ ዋጋ እንድታገኝ በማድረግ ረገድ እንደሚጠቅማት ብታውቅም ከግብፅ ጋር በፈጠረችው ጊዜያዊ የፖለቲካ ትብብር ምክንያት ድርድሩ እንዲስተጓጎል እየሠራች እንደምትገኝም ገልጸዋል።