ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ትግራይ ውስጥ ተይዘው ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ የተደረጉት ከፍተኛ የህወሓት አመራሮች የቀረበባቸውን ክስ አልፈጸምንም ሲሉ ካዱ።
ትናንት ፍርድ ቤት ከቀረቡት ከፍተኛ የህወሓት አመራሮች መካከል አቶ ስብሐት ነጋንና ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂምን ጨምሮ በርካታ ግለሰቦች የተካተቱ መሆኑም ታውቋል።
በቁጥር ሃያ የሚደርሱት እነዚህ የህወሓት አመራሮች አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኘው የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት የቀረቡ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል የህወሓት ቀደምትና ከፍተኛ አመራሮች የነበሩት አቶ ስብሃት ነጋ፣ አቶ አባይ ወልዱ፣ ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም፣ አብርሃም ተከስተ (ዶ/ር)፣ ወይዘሮ ቅዱሳን ነጋ፣ ወ/ሮ ሙሉ ሙሉ ገብረእግዚአብሔር እና አቶ አባዲ ዘሞ እንደሚገኙበት ለማወቅ ተችሏል።
ተጠርጣሪዎቹ በዋናነት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ ሕገ ወጥ ቡድን አደራጅተው በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት እንዲፈጸም በማድረግ፣ ወጣቶች ለጦርነት እንዲዘምቱ በመቀስቀስ፣ የነዳጅ ማከማቻዎች እንዲዘረፉ በማድረግ፣ የበርካታ የመከላከያ ሠራዊቱ አባላት ህይወት እንዲጠፋ አድርገዋል የሚል ክስ ተመስርቶባቸዋል።
በሕግ ባልተሰጣቸው ሥልጣን ከተለያዩ ሀገራት ጋር ግንኙነት በመፍጠር፣ ለጦርነት ገንዘብ መሰብሰብ፣ በጎንደርና በባሕር ዳር ከተሞች ውስጥ በሚገኙ አውሮፕላን ማረፊያዎች ላይ ሮኬት እንዲተኮስ እና የንጹሃን ህይወት እንዲጠፋ በማስደረግ የተሰኙ ወንጀሎች ላይ መሳተፋቸውን የፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቡድን ለፍርድ ቤቱ አብራርቷል።
የህወሓት አመራሮቹ በፖሊስ የቀረቡባቸውን የወንጀል ክሶች በሙሉ አልፈጸምንም ሲሉ ጉዳያቸውን ላደመጠው የፌደራል ፍርድ ቤት የገለጹ ሲሆን፤ ፖሊስም ተጨማሪ ምርመራ ለማድረግ የ14 ቀን ጊዜ ቀጠሮ ጠይቆ ተፈቅዶለታል።