ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ወደ ቀደመ ሰላሟ መመለስ ባልቻለችው ትግራይ ክልል በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በረሃብ ምክንያት ለሞት ሊዳረጉ ይችላሉ ተባለ።
ከእርዳታ ሠራተኞች ጋር ከተደረገ ስብሰባ ላይ አንድ ባለሥልጣን እንዲህ ማለታቸውን ያረጋገጠው ሾልኮ የወጣ ማስታወሻ ላይ የሰፈረ ጽሑፍ መሆኑን የዘገበው ቢቢሲ ነው።
ታኅሣስ 30/2013 ዓ.ም በትግራይ የአስቸኳይ ጊዜ ማስተባበሪያ ማዕከል አማካይነት በተካሄደው ስብሰባ ላይ በአንድ ተሳታፊ አማካይነት የተነሱ ነጥቦች የሰፈሩበት ማስታወሻ፤ በስፍራው ያለው ሁኔታ በጣም የከፋ ነው ሲል ችግሩ አሳሳቢ ደረጃ መድረሱን ጠቁሟል።
“ምግብና ምግብ ያልሆኑ ነገሮች ወይም ሌሎች ለኑሮ መሰረታዊ የሆኑ ነገሮች ተዘርፈዋል ወይም ወድመዋል። እንደሁም አስቸኳይ እርዳታ ካልቀረበ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በረሃብ ሊሞቱ ይችላሉ።” ያለው የባለሥልጣኑ ማስታወሻ፤ “የተለያዩ ቦታዎችን ለመጎብኘት በተጓዝንበት ጊዜ አብረውን የነበሩ አጃቢዎቻችንን ብስኩት ይጠይቋቸው ነበር” የሚል ጽሑፍም አካቷል።