ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት እንዲፈጸም መረጃ አቀብለዋል የተባሉት የምስራቅ ዕዝ 12ኛ ክፍለ ጦር ሓላፊ ኮሎኔል ምሩፅ ወ/አረጋይ ዛሬ ፍርድ ቤት ቀረቡ።
ተከሳሽ ድርጊቱን ለመፈጸማቸው የሚያሳይ ማስረጃዎችን ማሰባሰቡን ለፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት የገለጸው መርማሪ ፖሊስ፤ ከዚህ በተጨማሪ የትግራይ ተወላጅ ያልሆኑ የምስራቅ ዕዝ አባላት ጉዳት እንደደረሰባቸው ለማድረግ የታለመ ሥራ ስለመስራታቸውም መረጃው አለኝ ብሏል።
” ፖሊስ አገኘሁት ያለው ማስረጃ የእጅ ስልኬን ብቻ ነው እሱን ደግሞ መርምሮ ማስረጃ አሰባስቦ ክስ ሊመሰርት ይችል ነበር በጥርጣሬ ብቻ ነው የታሰርኩት” በማለት የተናገሩት ተጠርጣሪው፤ በተጨማሪም የተባለውን ወንጀል አለመፈፀማቸውን እና በሓፊነት ሥራቸውን ሲከውኑ እንደነበር ለችሎቱ ገልጸዋል።
ጉዳዩን የተከታተለው ፍርድ ቤት መርማሪ ፖሊስ ተጨማሪ ማስረጃዎችን እንዲያሰባስብ እና የምርመራ ሥራውን እንዲቀጥል ተጨማሪ 14 የምርመራ ቀናት በመፍቀድ ለጥር 26፣ 2013 ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱ ተሰምቷል።