ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የሱዳን ሽግግር መንግሥት ፕሬዝዳንት የሆኑት ሌፍተናንት ጀነራል አል ቡርሀን ሀገራቸው ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር ጦርነት ውስጥ መግባት እንደማትፈልግ ገለጹ።
ፕሬዝዳንቱ ይህንን የተናገሩት ከአገሪቱ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ ሲሆን፤ አገራቸው ሕጋዊ መብቷን በሚያስከብር መንገድ አሁን በሱዳን ሠራዊት የተያዙት ቦታዎች ስምምነት ላይ እንዲደረስ ፍላጎታቸው እንዳላቸውም አብራርተዋል።
በአሁኑ ወቅት የሱዳን ሠራዊት የተሠማራበት አካባቢ የአገሪቱ ግዛት ነው ያሉት ጀነራሉ፤ ጦር ሠራዊታቸው ይህንን እርምጃ የወሰደው በሱዳን መንግሥት ውስጥ ካለው ፖለቲካዊ አካል ጋር በተደረገ ሙሉ ቅንጅት ነው ሲሉ ተደምጠዋል።
ጄኔራሉ ሱዳን ጦርነትን አትፈልግም ቢሉም ከደነበራቸው ሽራፊ መሬት አሳልፈው እንደማይሰጡም ዝተዋል።
ሱዳን በትግራይ ክልል የትህነግ አመራሮች ላይ በተወሰደው ህግን የማስከበር ዘመቻ ማግስት የኢትዮጵያን ድንበር ጥሳ በመግባት አርሶ አደሮችን በማፈናቀል መሬት የተቆጣጠረች መሆኑ ይታወሳል።