በጋምቤላ ታዳጊዎች ሕፃናት ኦነግ ሸኔ ናችሁ በሚል ታስረው መደብደባቸው ተጋለጠ

በጋምቤላ ታዳጊዎች ሕፃናት ኦነግ ሸኔ ናችሁ በሚል ታስረው መደብደባቸው ተጋለጠ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– በጋምቤላ ክልል ያለው የሰብኣዊ መብት አያያዝ በእጅጉ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ገለጸ።

በክልሉ የታሳሪዎች አያያዝ ሊሻሻል ይገባል ያለው ኮሚሽኑ  የተቃዋሚ ፓርቲዎችም በነጻነት የመንቀሳቀስ መብት ሊከበርላቸው እንደሚገባ ጠቁሟል።

 በጋምቤላ ክልል አኝዋ ዞን ከታኅሣሥ 12 እስከ 15 2013 ጉብኝት ማድረጉን የገለጸው የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብት ኮሚሽን፤ በጎበኛቸው የክልሉ ማረሚያ ቤቶች በእስር ላይ የሚገኙ ሰዎች አያያዝና ሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ሁኔታ በአፋጣኝ ሊሻሻል የሚገባው እንደሆነ ተመልክቻለሁ ብሏል።

 የኦነግ ሸኔ አባላት ናቸው ተብለው ተጠርጥረው በእስር ላይ ያሉ የ11 እና 12 ዓመት ወንዶች፣ እንዲሁም የ14 ዓመት ታዳጊ ሴት መመልከቱ እጅጉን እንዳሳሰበው የጠቆመው ኢሰማኮ ፤ ታዳጊ ወንዶቹ በእስር ላይ ሳሉ ድብደባ እንደተፈጸመባቸው ጠቁሞ፣ በአሁኑ ወቅት በእስር ላይ የሚገኙት ታዳጊዎች በአስቸኳይ ከእስር እንዲለቀቁ እና የደረሰባቸው ጥቃት ላይም ምርመራ እንዲደረግ የክልሉን አስተዳዳሪዎች ጠይቋል።

“የጋምቤላ ክልል መንግስት ትኩረትን የሚሹ በርካታ ጉዳዮች መኖራቸው የሚታወቅ ቢሆንም፣ የሕፃናት እስረኞችና የተጠርጣሪ ታሳሪዎችን የዋስትና መብት ማረጋገጥ እጅግ አፋጣኝ ትኩረት ይሻል” ያሉት የኮሚሽኑ ሊቀመንበር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ፤ ሀገራዊ ምርጫው እየተቃረበ በመሆኑ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በነፃነት የሚንቀሳቀሱበትን ዕድል የክልሉ መንግሥት መፍጠር ይገባዋል ብለዋል።

በሌላ በኩሌ የትግራይ ተወላጆች የሆኑ እና ለህወሓት ድጋፍ በማድረግ ተጠርጥረው የታሰሩ 90 እስረኞችን በሁለት እስር ቤቶች ውስጥ ማግኘቱን ያጋለጠው እና በዶክተር ዳንኤል በቀለ የሚመራው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን፤ ግለሰቦቹ ከኅዳር 5 ጀምሮ በእስር ላይ እንደሚገኙና  በእስረኞቹ ላይ እስካሁን ድረስ ምንም አይነት የምርመራ ሥራ አለመጀመሩን ይፋ አድርጓል።

LEAVE A REPLY