ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የትህነግ ቡድን ህግን በመጣስ ብሎም ሀገርን በመካድ የፈፀመውን ወንጀል የሚያሳይ የምርመራ ውጤት ዛሬ ይፋ አድርጓል።
በመቐለ፣ በማይካድራ እና በሌሎች አካባቢዎች ያደረሰውን ሰብኣዊ ጥሰት፣ የፌዴራል መንግሥትን አደጋ ላይ በመጣል እና ሀገርን በመካድ ወንጀል የተሰማሩ አካላትን ላለፉት 3 ወራት ግብረሀይል በማቋቋም ሲመረምር መቆየቱን የገለጸው ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ፤ በዚህም 253 የሚደርሱ ተጠርጣሪዎች እንደነበሩ፣ ተጠርጣሪዎቹ ጡረታ የወጡ እና ከፀጥታ ተቋማት ከድተው ሀገርን በማፍረስ በወንጀል የተሰማሩ እንደሆኑም ለማወቅ ተችሏል ብሏል።
ከተጠርጣሪዎቹ መካከል 96 የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች የሚገኙበት ሲሆን፣ ህቡዕ የሆነ ፅንፈኛ ቡድን በማደራጀት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ መቆየታቸውንም የፌዴራል ፓሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምርመራ ቢሮ ም/ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ጠቁመዋል።
ሀገርን ለማመስ ተደራጅተው ሲንቀሳቀሱ የቆዮ በስልጣን ላይ የነበሩ፣ እንዲሁም በጡረታ ላይ የነበሩ 349 ተጠርጣሪዎች መኖራቸውን እና፣ 124ቱ በቁጥጥር ስር ሲውሉ የተቀሩት በህግ ማስከበር ሂደቱ መደምሰሳቸውን ለማወቅ ተችሏል።