ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የአማራ ሕዝብ ንቅናቄ (አብን) ዛሬ በኦሮሚያ ከተሞች ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ድጋፍ በተካሄደው ሰልፍ ላይ በአደባባይ ተወገዘ።
“በጨለመባቸዉ በአብን፣ በኦነግ ሸኔ እና በጽንፈኞች ምክንያት ኢትዮጵያ አትፈርስም” የሚል ንግግር ያሰሙት የሰበታ ከተማ ከንቲባ አቶ ብርሃኑ በቀለ፤ ለዶ/ር ዐቢይ አህመድ በሰበታ ከተማ በተካሔደዉ ሕዝባዊ
የድጋፍ ሠልፍ ላይ የጁንታዉ ተላላኪ በሆኑት በአብንና በኦነግ ሸኔ ምክንያት የምትፈርስ ሃገር አትኖርም ሲሉ ተደምጠዋል።
የጁንታዉ ተላላኪዎች ዋና ዓላማ ሕዝብን ከሕዝብ በማጋጨት ለዉጡን ማደናቀፍ ነዉ ያሉት ከንቲባዉ በዉድ ዋጋ የተገኘዉ ድል በጽንፈኞችና በጁንታዉ ተላላኪዎች ሴራና ተንኮል አይደናቀፍም በማለት አብንን የጁንታው ተላላኪ ያደረጉበት መንገድ በሕዝብ ዘንድ ግርምትን ፈጥሯል።
በተያያዘ የከተማዉ የብልጽግና ፖርቲ ሓላፊ አቶ ዋቀዮ አላኬ በበኩላቸዉ፤ ጽንፈኞች የኢትዮጵያ ሕዝብ
ጠላቶች ስለሆኑ መላዉ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብንንና ኦነግ ሸኔን መዋጋት አለበት የሚል እና ሥርዓቱ በአማራ ሕዝብ ላይ ያለውን የመረረ ጥላቻን ያመለከተ ንግግር አድርገዋል።
የአመራሮቹን አማራ ብሔር ላይ ያተኮረ እና ሆን ተብሎ የተላለፈ መልዕክትን ያሠራጨው ኦቢኤን ቴሌቪዥን፤ በተመሳሳይ ኦነግ ሸኔ እና አብን የኦሮሞንና የአማራን ሕዝብ የማይወክሉና የሕዝቦችን አብሮ መኖር የማይሹ
ጽንፈኞች ስለሆኑ እናወግዛቸዋለን የሚሉ የከተማዋ ነዋሪዎችን የወከሉ ግለሰቦችን አስተያየት ሲያስተላልፍ ለመታዘብ ችለናል።

























