ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በሱዳን ድንበር ዙሪያ ያለውን ውጥረት ለመፍታት ኢትዮጵያ የሦስተኛ አካል ጣልቃ ገብነትን እንደማትፈልግ አቶ ውሂብ ሙሉነህ በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ከድንበር ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ቴክኒካል አማካሪና በኢትዮጵያ ሱዳን ድንበር ኮሚሽን አባል አስታወቁ።
ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር ያለውን የድንበር አለመግባባት ውዝግብ በውይይት ብቻ ለመፍታት ጥብቅ ፍላጎት አላት ያሉት አቶ ውሂብ፤ ሱዳንም ብትሆን እስካሁን ድረስ በሁለትዮሽ ንግግር ችግሩን መፍታት እና የሦስተኛ ወገን አደራዳሪነትን እንዲኖር ሀሳብ አለማቅረቧን ገልጸዋል።
ሁለቱን ሀገራት ለማስታረቅ እና ለማሸማገል የተለያዩ አካላትም ጥረት እያደረጉ ሲሆን ፤ ጉዳዩ ያሳሰባት የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ኢትዮጵያና ሱዳን ያላቸውን የድንበር ላይ ውዝግብ በሰላማዊ መንገድና በውይይት እንዲፈቱ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሯ በኩል ባወጣችው መግለጫ መጠየቋ ይታወሳል።