ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አቶ ጃዋር መሐመድ፣ አቶ በቀለ ገርባ፣ አቶ ሀምዛ አዳነ(ቦረና) እና አቶ ሸምሰዲን ጣሃ ከጥር 19፣2013 ዓ/ም ጀምሮ በረሃብ አድማ ላይ እንደነበሩ አረጋገጠ።
“መንግሥት በሕዝብና በፓርቲያቸው ላይ እያደረሰ ያለውን አፈናና የመብት ጥሰት ለመቃወም፣ የኮሎኔል ገመቹ አያናን አላግባብ የሆነ አያያዝ እና እንግልት እንዲቆም ለመጠየቅ እና የችሎት ሂደታቸውን ለመከታተል ወደ ፍርድ ቤት በሚመጡ እና እነርሱን ለመጠየቅ ወደ ማረሚያ ቤት በሚመጡ ሰዎች ላይ የሚፈጸም እስር እና ወከባ እንዲቆም ለመጠየቅ” የረሃብ አድማው እንደተደረገ እስረኞቹ ነግረውኛል ሲል ኮሚሽኑ አስታውቋል።
የቃሊቲ ማረሚያ ቤት አስተዳደር በበኩሉ ለረሃብ አድማው በምክንያትነት የተጠቀሱ አብዛኛዎቹ ጉዳዮች ማረሚያ ቤቱን የማይመለከቱ መሆኑንና እስረኞችን ለመጠየቅ የሚመጡ ሰዎች ላይ ወከባ እንደማይፈጽም ምላሽ ሰጥቷል።
አስተዳደሩ አክሎም የረሃብ አድማው በእስረኞቹ ላይ የከፋ ጉዳት እንዳያስከትል፣ በተለይም ከመካከላቸው ሁለቱ የጤና ችግር ስላለባቸው በቋሚነት መድኃኒት የሚወስዱ በመሆኑ ቅርብ የህክምና ክትትል እንደሚደረግላቸው አስረድቷል።