ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– “የመማር ማስተማር ሂደቱ እንዳይቋረጥ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛዬን እጠቀማለሁ” በሚል መሪ ቃል ሀገር ዐቀፍ የ“እንድናገለግልዎ ማስክ ያድርጉ” ንቅናቄ በዛሬው ዕለት በትምህርት ቤቶች በይፋ ተጀመረ።
የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን ለመከላከል የሚደረገው ንቅናቄ ከዛሬ ጀምሮ በሀገር ዐቀፍ ደረጃ በሁሉም ትምህርት ቤቶች ተግባራዊ እንደሚደረግ የተገለጸ ሲሆን፤ ይህም የመማር ማስተማሩ ሂደት እንዳይቋረጥ እና ትምህርት ቤቶች እንዳይዘጉ፣ በትምህርት ቤት ውስጥ እና ከትምህርት ቤት ውጪ ተማሪዎች የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛን በአግባቡ እንዲጠቀሙም በፕሮግራሙ ላይ ሠፊ ገለጻ ለመስጠት ያስችላል።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ የኮሮና ቫይረስ ሥርጭት በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋ ቢገኝም፤ ሕብረተሰቡ ላይ ግልጽ የሆነ የመዘናጋት ስሜት እየተስተዋለ ነው።