ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ሱዳን በድንበር የተነሳ ወደ ጦርነት እንድንገባ የመከላከያ ኃይሏ ከፍተኛ ግፊት እያደረገ ነው ሲል የኢትዮጵያ መንግሥት ሱዳንን ወነጀለ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ በሁለቱ አገራት መካከል ካለው የድንበር አለመግባባት አንጻር ሱዳን እየተከተለችው ያለውን ችግሩን አባባሽ ጸብ አጫሪ እርምጃን ነው ብሏል።
ኢትዮጵያ የትኛውም ግጭት የሁለቱን አገራት ደኅንነት የሚጎዳና ከባድ ጉዳትን የሚያስከትል መሆኑን ትረዳለች ያለው መግለጫ፤ የሱዳን መንግሥት ወታደራዊ ክንፍ እየተበረታታ ያለው ግጭት “በሱዳን ሕዝብ ኪሳራ የሦስተኛ ወገንን ፍላጎት የሚያስፈጽም ነው” በማለት እንቅስቃሴውን አጣጥሎታል።
የድንበር ጥያቄው ሊስተናገድባቸው የሚችሉ በቂ መንገዶች ቢኖሩም “የሱዳን ሠራዊት ዓለም ዐቀፍ ሕጎችን በመጣስ በኢትዮጵያ ላይ ወረራ ፈጽሟል” የሚለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መግለጫ፤ በሁለቱ አገራት መካከል ካለው የትብብርና የወዳጅነት መንፈስ በተቃራኒ የሱዳን ሠራዊት ንብረቶችን ዘርፏል፣ ካምፖችን አቃጥሏል፣ በሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን በማጥቃት እንዲፈናቀሉ በማድረግ፤ ባዷቸውን የነበሩ የኢትዮጵያ ሠራዊት ካምፖችን ተቆጣጥሯል ሲል እውነታውን አስረድቷል።
በመሆኑም አሁን ያለውን ወደ ጦርነት የመግፋት ዝንባሌና ግልጽ ወረራን በተመለከተ የአፍሪካ ሀገራት ሱዳንን አጥብቀው ይምከሩልኝ ስትል ኢትዮጵያ አሳስባለች።