ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀነራል ብርሃኑ ጁላ የተመራ የመከላከያ ሚኒስቴር ከፍተኛ የልኡካን ቡድን በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጉብኝት እያደረገ መሆኑ ተነገረ።
ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ከአቡዳቢ አልጋ ወራሽ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ አዛዥ ልዑል ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን ጋር ተገናኝተው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ የተላከ መልዕክት አድርሰዋል።
በኢትዮጵያና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መካከል ያለው ግንኙነት በሁሉም ዘርፍ እየተጠናከረ በመምጣቱ መጠን በሁለቱ አገራት የመከላከያ ተቋማት ያለው ግንኙነት በዚያው ልክ እየተጠናከረ፣ የትብብር አድማሱም እየሰፋ መሄዱን ጀነራል ብርሃኑ ጁላ አስረድተዋል።
ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ በቀጣይ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የመከላከያ ሚኒስትር እና ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጋር ተገናኝተው ይወያያሉ ተብሏል።