የውይይቱ መንሥኤ፤
“የኦሮሞ እና የአማራ እውነተኛው የዘር ምንጭ” ብለህ የጻፍከው፥ እውነተኛው የዘር ምንጭ አይደለም ጥሩ ተረት ነው ብየ ምክንያቴን ብሰጥ ቁጣህ ከመጠን አልፎ ስድብ ውስጥ ገባህ። “ተረቴን እንደታሪክ አልቀበል ያልክ ሁሉ ጌታቸው የደረሰበትን አይተህ ተቀጣ” ማለትህ ይመስላል። ውይይታችን በመጽሐፍህ ውስጥ ስላካተትካቸው ሐሳቦች እንጂ፥ አንተንና አንዳንድ አራጋቢዎችን እንደመሰላችሁ፥ ስላንተ ወይም ስለኔ አይደለም። እኔ ማስረጃ ይዤ ተረቶች ናቸው ያልኳቸውን አስተዋፅኦችህን አንድ በአንድ ከነማስረጃዬ ዘርዝሬያለሁ፤ ጉዳያችን ያለው እዚህ ላይ ነው። ለናሙና ያህል ከዘረዘርኳቸው ዓሥራ ሦስት ስሕተቶች ውስጥ የአማራው ሕዝብ አባት የተፀነሰው እባሕር ውስጥ ነው ያልከው ስሕተት ይገኝበታል። ስሕተቶች ያልኳቸውን ስሕተቶች አለመሆናቸውን አንድ ባንድ እንድታስረዳ አንባቢህ ይጠብቃል። እውነተኛ ታሪክ ለመሆናቸው ማስረጃው ስድብና ውሸት አይደለም። መልስ መስጠት ካልቻልክ አፍረህና አርፈህ ዝም በል። ማፈርና መልስ አለመስጠት መብትህ ናቸው።
ስሕተቶችህን ማንሣቴን “በቂም በቀል መፅሃፉን ለማጠልሸት” ያደረግሁት አድርገህ ጽፈሃል። ምን ጥቅም ፈልጌ ያንተን ሥራ አጠለሻለሁ? አስተማሪ ስለሆንኩ ተማሪዬና የተማሪዬ ተማሪ (የኔ ተማሪ ዮናስ አድማሱና የዮናስ ተማሪ አንተ) በሙያችሁ አሸብርቃችሁ ሳይ እኮራባችኋለሁ እንጂ፥ ሥራችሁን አላጠለሽም። ውረድ ተዋረዱ የሚመሰክረው “ደቂቀ ጌታቸው” መሆናችሁን ነው። ቂሙና በቀሉ መንሥኤ የሌለው ክስ ነው። ከእኔ ሌላ በታሪክ ዕውቀታቸው የተከበሩ ሌሎች ሰዎችም በመጽሐፍህና በምንጭህ ቅሬታቸውን ገልጸዋል። የርዕዮት ጠያቂ ቴዎድሮስ ጸጋዬም ሥራህን የነቀፈው አሸዋ ላይ የተመሠረተ ቤት ሆኖ ስላገኘው ነው። ንቀው ካልተውህ፥ ወይም በኔ ላይ ያወረድከው የስድብ ናዳ እንዳይደርስባቸው ካልፈሩ፥ ሌሎችም ሊነሡ ይችላሉ፤ ታዲያ እነሱ ሁሉ ቂም በቀል ያላቸው ሊሆኑ ነው ወይስ እኔ ብቻ ነኝ ቂመኛውና በቀለኛው?
መጽሐፍክን ያልወደድኩበት ምክንያት፤
ልብ ሳትለው አንዳልቀረህ ባውቅም፥ መጽሐፍህን ያልወደድኩት፥ የታላቁ ታሪካችንን ክብር ስለነካ ነው። “ቅናት ነው” ካልከውም፥ ስለ “ቅንዑ ለእንተ ተዓቢ ጸጋ” እንጂ፥ ሥራህስ ያሳፍራል እንጂ አያስቀናም። የኢትዮጵያን ታሪክ በጠቅላላው “የጠነዙ ገለፃዎች” ከሚለው ካንተ የታሪክ መጽሐፍ ይልቅ፥ “ኢትዮጵያ የአንድ መቶ ዓመት ታሪክ ያላት አገር ናት” የሚሉት ይሻላሉ። እኔም ለአምላክ ክብር ይግባውና ማስረጃው እያለኝ፥ እነሱም ሆኑ አንተ የተከበረውን ታሪካችንን የልጆች አእምሮ የሚያበላሽ ተረት ልትተኩት ስትሞክሩና ተቀባይነት ስታገኙ ሳይ ዝም አልልም። መጽሐፋችንም፥ “ተባአስ በእንተ ጽድቅ እስከ ትበጽሕ ለሞት” (ለሞት እስክትደርስ ድረስ ስለ እውነት ተጋፈጥ) ይላል። ከዓለም አቀፍ ምሁራን ጋራ ያለኝን ግንኙነት ክፉ ትርጕም ሰጥታችሁታል። እነሱ ግን፥ ከፖለቲከኞቹና ከሰላዮቹ በቀር፥ ታሪካችንን የሚማሩትና የሚጽፉት የታሪካችን ክብር ስለሳባቸውና ከክብሩም ለመካፈል ነው።
መሪራስ አማን በላይ፤
ከመሪራስ አማን በላይ ያመጣህልኝ መልክትም አለህ። የተጋለጠ ሰው ስድብ ሆነ እንጂ፥ መልእክቱስ ያልተጠባበቅሁት አይደለም። ሰውየው ውሸተኛ አደረከኝ ብሎኝ ተቆጥቶ ሳለ፥ አለመዋሸቱን በማስረዳት ፈንታ፥ በውሸት ላይ ውሸት አከለበት። አንደኛ፥ “ፈንታሁን ጥሩነህን አማላጅ ልከህብኝ ነበር” ብሎ፥ እውነቱ ሲገለጥ የሚያሳፍር አዲስ ውሸት ጨመረበት። ለነገሩማ፥ አዲስ ጽሑፍ ተገኘ ሲባል የኔ ብጤው ተመራማሪ ለማየት ቢጓጓ አያስገርምም። ግን መሪራስ አማን በላይ አገኘሁት ስላለው የብራና ጥቅል መጽሐፍ ጉዳይ አቶ ፈንታሁንን እንኳን አማላጅ ልልከው፥ በጉዳዩ ጨርሶም አልተነጋገርንበትም። ለማረጋገጥ የፈለገ አቶ ፈንታሁንን መጠየቅ ይችላል። ይህም ጽሑፍ በይፋ ሲወጣ አቶ ፈንታሁን ያየዋል።
ሁለተኛ፥ “የሱባንና የግዕዝ መዝገበቃላትን ለቤተ መጻሕፍት ወመዘክር አንዳንድ ቅጂዎች አበርክቻለሁ፡ . . . የብራናዎቹን ቅጂዎች በመስጠቴ ቤተመጻህፍት ወ መዘክር መቀበሉን የሚያንጸባርቅ የምስክር ወረቀት ሲሰጠኝ የኬነዲ ቤተመጻሀፍት ግን አመሰግናለሁ እንኩዋን አላለኝም” ይላል። ይኸንን ሳነብ ሰውየው የሚጽፈው የተለመደውን ውሸት ይሁን እውነት ለማረጋገጥ ሞክሬ ነበር። ያገኘሁት መልስ ዩኒቨርስቲውም ብሔራዊ ቤተ መጻሕፍትም መሪራስ አማን በላይ የሰጠው የብራና ጽሑፍ የለም የሚል ነው። የተጻጻፍኩትን ለገለልተኛ ሰው ላሳይ እችላለሁ። ደግሞም ማንም ሰው በግሉ መጠየቅም ይችላል። መሪራስም የተሰጠውን የምስክር ወረቀት ቢያሳየን ምን ሰነድ እንደሰጠ ልንረዳ እንችላለን። አልነጥቀውም።
ሌላው ከመሪራስ ያመጣኸው መልእክት የሚነግረን “በግዕዝ የተጻፉ የብራና መጻሕፍት ጥቅሎች” እንጂ በሱባ ቋንቋ ስለተጻፈ መጽሐፍ የሚመሰክር ቃል አይደለም። አየኸው፥ ዶክተር ፍቅሬ፥ ሰውየው ከዳህ እኮ። በመጽሐፍህ ሽፋንና በውስጡም ገጽ84-89 ስላወጣኸው የሱባ መጽሐፍ አንዳች ቃል አልተናገረም። ይኸንን ሳነብ የ “እስከ ማእዜኑ” ተንኮል ትዝ አለኝ። ስሜ “እስከ ማእዜኑ” (እስከ መቸ ድረስ) ነው የሚባል ሰይጣን ነበር ይላል መጽሐፈ ቀሌምንጦስ። ለተንኮል፥ ከአንድ ሰው ጋር ተወዳጅቶ ክፋት ሲያሠራው ኖሮ፥ አንድ ቀን ወዳጁ ድንገት መሬት ሲናድበት እንዲረዳው፥ “እስከ ማእዜኑ” ብሎ ጠራው። አጅሬ፥ “እስከ ይእዜ” (እስከዚህ) ነው ብሎ ገፍትሮ ከገደል ጣለው ይላል።
የብራና የግዕዝ መጻሕፍትማ በየቦታው ይገኛሉ። ባለፈው ወር እንኳን ከዚህ በታች ያለውን ዜና ሰምተናል፤
Catholic University Receives Donation of Ethiopian Manuscripts Valued at More Than $1 Million.The Catholic University of America is now home to one of North America’s most important collections of Ethiopian religious manuscripts, thanks to a generous donation from Chicago collectors Gerald and Barbara Weiner. The handmade manuscripts, which originate from Ethiopia and which date back to the eighteenth and nineteenth centuries, include more than 125 Christian manuscripts, 215 Islamic manuscripts, and 350 “magic” scrolls.
መሪራስ አማን በላይ የግዕዝ ችሎታውን ሳልጠራጠር፥ ስለ ግዕዝ ችሎታው ሰፋ ያለ መልእክት አመጣህልኝ። ስለችሎታው እንድትነግረኝ የላከህ ለምን ይሆን? ወይ ራሱን ተጠራጥሯል ወይም “አንድ ያላት እንቅልፍ የላት” ሆኖበታል። ግዕዝ ማወቂያውን መንገድም ወደ መንግሥተ ሰማያት እንደሚያደርስ መንገድ አንድ ብቻ የመሰለው፥ በዕውቀት ጉድለት ምክንያት ነው። ለምሳሌ፥ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ “መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ፥ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ” በሚል ርእስ ያሳተሙት ስመ ጥር መጽሐፍ የማንን ሥራ ተርጕመው እንደሆነ ቢያውቅ ኖሮ፥ መንገዱ አንድ እሱ የሚያውቀው ብቻ አለመሆኑን ዐውቆ ዝም ይል ነበር። የመዝገበ ቃላቱ ደራሲው እንኳን የኢትዮጵያን ገዳማት አገሪቷንም ቢሆን በአካል አያውቃትም።
“እኝህ ሰው [አማን በላይ] እጃቸው ውስጥ የከበሩ ብራናዎች እንደ አሉ እርስዎም ጠንቅቀው ያውቃሉ” ብለኸኛል። ያልኩት ተምታታብህ መሰለኝ፤ በአድያም ሰገድ ኢያሱ ዘመን የተቀዳ ታሪከ ነገሥት ቅጂ እንዳለው ተናግሬያለሁ። ጀበል ኖባ አገኘሁ የሚለው የብራና ጥቅል ጽሑፍ ግን የለውም። እንዳለው እንኳን ጠንቅቄ ላውቅ፥ መጠርጠሬንም አቁሜያለሁ። ውሸቱን ነው። እሱም ነገረህ እኮ!!
ውድ ፕሮፌሰር ፍቅሬ፤ ወዳንተው ልመለስና፥ “ምንጬ የአማን በላይ ግኝት ብቻ አይደለም፤ ሌሎች 47 መጻህፍት አስፍሬያለሁ” ብለሃል። እውነት ነው፤ አስፍረሃል። ግን አንዳቸውም አዲሱን ትምህርትህን የሚደግፉ አይደሉም። አንዳቸውም የአማሮች አባት ከባሕር ወጣ የምትለውን ተረት አይደግፉም። እየሱስ ክርስቶስ ንግሥት ሳባን “የአዘቦ ንግሥት አላት” የምትለውን ተረት አይደግፉም፤ የአክሱም ነገሥታት ሜሶፖታሚያ ድረስ ያስገብሩ ነበር የምትለውን ተረት አይደግፉም። መጻሕፍቱን የጠቀስካቸው “የጠነዙ ገለፃዎች” ብለህ ለመንቀፍና ከእነሱ ለመራቅ እንጂ ተረትክን እንዲደግፉልህ አይደለም። በእነሱ “ላይ ተመስርቼ አዘጋጅቻቸው የነበሩትን ጽሑፎች (የመሪራስ ግኝት) እንድከልስ አድርጎኛል” ካልክ በኋላ፥ አሁን ወደኋላ ተመልሰህ ለድጋፍ ጠቀስኳቸው ብትል ማን ያምንሃል? ተሳስቼ እንደሆነ፥ እስቲ ከ47ቱ መጻሕፍት እነዚህን ተረቶች የሚደግፍ አንድ መጽሐፍ ጥራልን።
ምስጋና ቢስ፤
መጽሐፍህ ውስጥ ስላሰፈርካቸው በጎ ሥራዎች አላመሰገንከኝም አልከኝ። “ምስጋናህ አልበቃኝም” ማለትህ ነው ወይስ ማመስገኔን ጨርሶ አላነበብከውም? “ዶክተር ፍቅሬ በአማርኛ ሥነ-ጽሑፍ ስም ያወጣ የምናደንቀው ደራሲያችን” ነው ያልኩት ከልቤ ነው። እውነተኛ ምሁር አለመስኩ ገብቶ ሲያሳስት ደግሞ የሚገባው ምስጋና ሳይሆን ስሕተቱን ማሳየት ነው። እኔም ያደረግሁት ይኸንን ነበር፤ እንደ እውነተኛ ምሁር አልተቀበልከውም። በሥራው የማይተማመን ሰው የሚሰጠውን መልስ ሰጠህ። ምክንያትህ ግልጽ ነው።
ፕሮፌሰር ኤድዋርድ ኡልንዶርፍ “ኦሮሞዎች ለኢትዮጵያ ስልጣኔ ያበረከቱት አስተዋጽኦ የለም” ማለቱን መንቀፍህን ሳላመሰግን ማለፌን አንሥተሃል። ዓላማህ በተናገርከው ጽድቅ ሁሉ እንደ ሕፃን ልጅ አመስግኑኝ ማለት ነው ወይስ ፈረንጅ ሲነካ አትወድም ለምትለኝ ስድብ ማስረጃ ማምጣትህ ነው? እኔ ግን ስለ ኡልንዶርፍ ስትጽፍ ያደረግከውን ስሕተት በዝምታ ያለፍኩት እዚህ ቦታ አውቆ አጥፊ አለመሆን በማየት ነበር። ካነሣኸው፥ የሆነውንና ያደረግኸውን ስሕተት ልናገር፤ አንደኛ፥ ፕሮፌሰር ኤድዋርድ ኡልንዶርፍ መሳሳቱን ያወቅኸው ከፕሮፌሰር ኤድዋርድ ኡልንዶርፍ መጽሐፍ ለመሆኑ የማያሻማ ማስረጃ አልሰጠህም። በግልጽ እንደሚታየው ከሆነ ግን፥ ያስተጋባኸው ዶክተር መሐመድ ሐሰን ከኡልንዶርፍ አሮጌው መጽሐፉ ውስጥ አግኝቶ የጻፈውን ነው። ፕሮፌሰር ኤድዋርድ ኡልንዶርፍ መሳሳቱ ተነግሮት ስሕተቱን በ1973 በሦስተኛው የመጽሐፉ ኅትመት አርሞታል። የታሪክ ዕውቀት አልባ መሆንክን ራስህ በራስል ላይ መሰከርክ። ምንጭህን ዶክተር መሐመድ ሐሰን ነው በማለት ፈንታ E. Ullendorf (sic), The Ethiopians, p. 7, ብለህ አልፈኸዋል። ዶክተር መሐመድ ሐሰን ተሳስቶ ያሳሳተህ፥ የ1960 ዓ. ም.ን፥ ቀኑ ያለፈበትን ያልታረመውን ኅትመት ጠቅሶ ነው። “በአምኀየስ ጊዜ የደነቆረ ዛሬም በአምኀየስ አምላክ” ይላል።
የተገናኘን ጊዜ ምን ተባባልን፤ በመልክና በስልክ በተገናኘን ጊዜ ስለተነጋገርነው ይጠቅምህ የመሰለውን እየመራረጥህ ጠቃቅሰሃል። ሌላውን አልጻፍከውም። እንደጀመርከው እንዳይቀር እኔ ልፈጽመው፤
ጽሑፎችህን እወዳቸዋለሁ ያልኩህ፥ ባህላችን አንድ መሆኑን ለማሳየት ከኦሮምኛና ከአማርኛ እውነተኛ ምሳሌዎች እያመጣህ ስለምትጽፍ ነበረ። አሁኑ መጽሐፍህ ውስጥም ብዙ ምሳሌዎች እንደሚገኙበት ተናግሬያለሁ። አሁን ግን ተለወጥክብኝ። በሰበሰብከው እውነተኛ ምሳሌዎች ላይ ሌላ የሌለና የማያስፈልግ ነገር አለ የማለት አመል አመጣህ።
አንድ ጊዜ በመልክ ስንገናኝ፥ ፕሮፌሰር ሪቺ የላከልህን ሰላምታ አምጥቼልህ፥ “ስለሱ Festschrift እየተዘጋጀ ነው፤ አንተስ ተሳታፊ ነህ ወይ” ብልህ፥ “ምንድነው ፌሽትሽሪፍት?’ አልከኝ። አንድ ምሁር፥ ያውም ጀርመንኛ አውቃለሁ የሚል፥ “ምንድነው ፌሽትሽሪፍት?’ ብሎ ሲጠይቅ ተገርሜ፥ “ፌሽትሽሪፍት” ምን እንደሆነ አታውቅም? ብየ ደጋግሜ ጠየኩህ፤ አንተም ደጋግመህ አላውቅም አልከኝ። የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ ሊቅ እንጂ የታሪክ ምሁር አለመሆንክንና በአንዳችም ፌሽትሽሪፍት ተሳትፈህ እንደማታውቅ አይቼ ነገሩን ችላ አልኩት። አሁን ልንገርህ፤ Festschrift ማለት ሊቃውንት የድርሰት አስተዋፅኦ እያደረጉ አንጋፋ የምሁር ጓደኛቸውን ለማክበር የሚያሳትሙት መጽሐፍ ነው። መጽሐፉ Festschrift in Honor Mr. X የሚል ርእስ ይዞ ይወጣል። ለመጀመሪያ ጊዜ ለአንድ ኢትዮጵያዊ ክብር የሚዘጋጀው መታሰቢያ Festschirft በቅርብ ጊዜ ስለሚወጣ አንድ ቅጅ ልልክልህ አስቤ ነበር። እንደማይጠቅምህ ገባኝ።
ደጋፊዎች እንዳሉህ ተረድቻለሁ። ስም እየለዋወጡ የሚመጡ ጥቂቶች ሊሆኑ ይችላሉ። አንድ ሰውማ አንተኑ ነው የጠረጠረው– ብዙ ፍቅሬ ቶሎሳዎች። አንዱ ደጋፊህ፥ “You made Dr. Fikre a laughing stock” ብሎ ወቀሰኝ። ራስክን መሳቂያ ያደረግኸው ራስህ ነህ። በግል የመከርኩህም፥ መሳቂያ እንዳትሆን ነበር። ከዚህ ቀደም ከአቶ አስቻለው ከተማ ጋር ያደረግኸውን ቃለ ምልልስ ሰምቼ ስልክ ደውየ፥ “መሪራስ በላይ አባይ የምትለው ሰው የሚለውን ይዘህ አትሳሳት፤ የሚናገረው እየፈጠረ ነው። ስምህ ይጠፋል” አልኩህ። አልሰማኸኝም። ጥቅም የምታገኝበት ወደመሰለህ ሄድክ።
ሌላው ውይይታችን የዘመነ መሳፍንት በር ከፋች ስለ ነበረው ስለ ራስ ሚካኤል ስሑል ላስተምራችሁ ብለህ የጻፍከውን ድርሰት የበተንክ ጊዜ ነው። መስፍኑን “ሚካኤል ስዑል” ስትለው፥ ታሪክ ዐዋቂ እንዳይነቅፍህ፥ አላዋቂውንም እንዳታሳስት በማለት፥ ስሕተትክን እንድታርም ነገርኩህ። እምቢ አልክ። የመስፍኑን የግዕዝ ታሪክ እንዳላነበብክው፣ ግዕዝም እንደማታውቅ ገባኝ። ታሪክና የግዕዝ ሥነ ጽሑፍ መስክህ ስላይደሉ እንዳትዋረድ ስለነሱ መጻፍ ምንም ቢያጓጓህ፥ ስትጽፍ በጥንቃቄ አድርገው። አንድ ጊዜ ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት የነገረኝ ድርጊት ትዝ አለኝ። ውሀ ዋና የሚችሉ ልጆች ተሰባስበው ለመዋኘት ወደ ቀበና ወንዝ ሲሄዱ በማህላቸው ዋና የማይችል ልጅ ኖሯል። ዋና የሚያውቁ ልጆች እየዘለሉ ውሀ ውስጥ ሲገቡ፥ እሱም ዘሎ ገባ። ያየው ጓደኞቹ ዘለው ሲገቡ እንጂ፥ ዘሎ ለመግባት የዋና ችሎታ እንደሚያስፈልግ ባለማወቁ ተጎዳ። ምክሬ፥ “እንዳትጎዳ እማታውቀው ውስጥ ዘለህ አትግባ” ነበር።
እየዋሸህ አትጥቀሰኝ፤
“አማን በላይ ከሱዳን አገር ያገኘው ምንም ነገር ስለሌለው ነው እንጂ፣ ቢኖረው ኖሮ እኔ የማውቃቸው ፈረንጆች መርምረው ምንነቱን ባረጋገጡ ነበር” ብለሃል አልከኝ። አላልኩም። ያልኩት እንደዚህ ነው፣
የጥቅሎቹ የመገኘት ታሪክ በዓለም በተከበሩ ምሁራዊ መጽሔቶች ላይ አንድም ቦታ ያልተነበበው ስለ [ሌለ] ነው። ሌሎቹ ቢቀሩ እንኳን፥ አዲስ አበባ የሚታተመው Journal of Ethiopian Studies እና የዶክተር ፍቅሬ ቶሎሳ ፒ. ኤች. ዲ. ፈታኝ የነበረው ፕሮፌሰር ሪቺ ናፖሊና ሮም ውስጥ ያሳትመው የነበረው Rassegna di Studi Etiopici ታሪኩ እውነት ሆኖ ቢያገኙት ተሽቀዳድመው በደስታ ያወጡት ነበር።
Journal of Ethiopian Studies እና Rassegna di Studi Etiopici ለኢትዮጵያ ታሪክና ሥነ ጽሑፍ ያበረከቱንን ከፍተኛ አስተዋፅኦ አታቅውም ማለት ነው።
ሁለተኛ፤ ባንተ ተስፋ ባልቈረጥኩበት ዘመን ስለ ክብረ ነገሥትና ስለ ንግሥተ አዜብ የጻፍኩት አጪር ድርሰት ሲታተም፥ የታሪክና የግዕዝ ሥነ ጽሑፍ ተመራማሪዎች እርስ በርሳችን እንደምናደርገው አንድ ቅጂ ልኬልህ ነበረ። በዚያ ጽሑፍ ያሰፈርኩትንና አሁን ደግሞ ስሕተትህን ስዘረዝር የጻፍኩትን በማጣመም፥ “ርስዎ ሳባን ስምዋን ቀይረው «ቢልቂስ« ብለው፣ በሃሰት ሳባ የኛ ቢልቂስ ናት ለሚልዋት ለአረቦች «ደ»ይሸልሙዋታል” ብለኸኛል። እኔ እንደዚህ ዝብርቅርቁ የወጣ ዐረፍተ ነገር አልጻፍኩም። “ሳባን ስምዋን ቀይረው” የሚለው አነጋገር የአላዋቂ ሐረግ ነው። “ሳባ” የመንግሥቷ፥ የግዛቷ ስም እንጂ አንተንና የታሪክና የግዕዝ መሃይምናንን እንደመሰላችሁ፥ የንግሥቲቱ ስም አይደለም። ስለማያውቁት መስክ መጻፍ ነፋስ ያለመንሽ የሚያነሣው ገለባ ይደርጋል።
እኔ ያልኩት እንደዚህ ነው፤ ብሉይ ኪዳን ስሟን ሳይጠራ “የሳባ ንግሥት” (በዕብራይስጥ “ማልከት ሽባ”) ብሎ ነው ያለፈው። ዐረቦች “ቢልቂስ” ይሏታል። ክብረ ነገሥቱ “ማክዳ” የሚለው እሷን ሊሆን ይችላል፤ ግን አጥጋቢ ማስረጃ የለንም።
ንግሥተ ሳባ፤
ዐዋቂውም አላዋቂውን እኩል የሚተችበት ኢንተርኔት ለማስተማሪያ እንደማያመች ብረዳም፥ ለመማር የሚፈልጉ ስለሚኖሩ ስለንግሥቲቱና ስለግዛቷ የታዘብኩትን በአጭሩ ላካፍል። ያልተስማማው “ተሳስተሃል” ቢለኝና ስሕተቴን ቢያሳየኝ ይበቃኛል። ስለ ማርያም፥ አትስደቡኝ።
“ንግሥተ ሳባ” ማለት “የሳባ ንግሥት”፥ “ሳባ የሚባል አገር የምትገዛ ንግሥት” ማለት ነው። ሐረጉ “ንግሥት ሳባ” ስለማይል፥ “ሳባ” የንግሥቲቷ ስም አይደለም። ስለንግሥቲቱ ዋናው ምንጫችን መጽሐፍ ቅዱስ ስሟን አልነገረንም። ስሟ አለመጠራቱ እና ኢየሱስ ደግሞ፥ እንደ ብሉይ ኪዳኑ “የሳባ ግንሥት” በማለት ፈንታ፥ “የደቡብ ንግሥት” ማለቱ፥ እንደ ፍቅሬ ቶሎሳ ላለው የክብረ ነገሥት ጸሐፊ የመሰለውን ለመጻፍ ክፍተት ፈጠረለት። የክብረ ነገሥቱ ደራሲ “የደቡብ ንግሥት” የሚለውን ይዞ፥ “ማክዳ፥ የምትባል የኢትዮጵያ ንግሥት ናት” አለን። የክብረ ነገሥቱ ጸሐፊ ሁለት ንግሥታት እንዳሉ አመነ ማለት ነው፤ አንዷን የሳባ ንግሥት፥ ሁለተኛዋን የደቡብ ንግሥት አድርጎ፥ የሳባ ንግሥትን ጨርሶ ረሳና የደቡብ ንግሥትን የኢትዮጵያ ንግሥት እያደረገ ጻፈልን። ስሟም ማክዳ ነው አለ። ንግሥተ ሳባን ጨርሶ የረሳት የየመን ንግሥት መሆኗን ማመኑ ነው። ክብረ ነገሥቱ የኛን ንግሥት “ማክዳ” እንዳላት የመኒዎች ደግሞ የነሱን ንግሥት “ቢልቂስ” አሏት። ሁለታችንም የየራሳችንን ንግሥት ይዘን እየሄድን ሳለ፥ በኋላ በማላውቀው ዘመን የተነሡ ሰዎች ወደኋላ ሄደው፥ “የኛይቱ ንግሥት ንግሥተ ሳባ ናት፤ ስሟም ማክዳ ነው” ብለው አዘባረቁ። ልድገመውና፥ ክብረ ነገሥቱ ንግሥተ ሳባን ጨርሶ አያነሣትም። የሰው አገር ንግሥት ምን ልታረግለት ያንሣት? ኢትዮጵያን የሷ ግዛት አላደረገም። እነአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ሁሉ ስለንግሥተ አዜብ እንጂ ስለንግሥተ ሳባ አልጻፉም።
ብሉይ ኪዳኑ “ንግሥተ ሳባ የሚላት የኛን ንግሥት ነው” የሚሉት ፥ “እውነት ከሆነ ለምን ንግሥተ ኢትዮጵያ አይላትም?” ወይም “ኢትዮጵያን ለምን ‘ሳባ’ አይላትም” ሲባሉ፥ አንዳንዶቹ “ኢትዮጵያ ሳባንም ትገዛ ስለነበረ ነው” ሲሉ አንዳንዶቹ ደግሞ “ሳባ ያለው አሰብን ነው” አሉ፥ ልክ ወዳጃችን “የአዘቦ ንግሥት” እንዳላት። እንደኔ ቢሆን፥ ክብረ ነገሥቱ እንደሚለው ንግሥተ አዜብ ትበቃናለች። እንዲያውም ከንጉሥ ሰሎሞን ልጅ ያረገዘችው ንግሥት አዜብ እንጂ ንግሥተ ሳባ አይደለችም።
እንደ እውነቱ ከሆነ፥ ሳባ ዛሬ “የመን” የትባለው አገር ናት። ዋና ከተማዋ ናግራን ይባል ነበር። ዳዊት፥ አንድ ቦታ ላይ፥ “ነገሥተ ሳባ ወዐረብ” (የሳባና የዐረብ ንጉሦች) ይላል። “ነገሥተ የመን ወዐረብ” (የየመንና የዐረብ ንጉሦች) ማለቱ ነው። በዚያን ጊዜ የመን ገና የዐረቦች አገር አልነበረችም። የዐረቦች አገር የሆነችው ከጊዜ ብዛት ነው፤ ልክ የፈርዖናውያን ግብጽ ዛሬ የዐረብ አገር እንደሆነች ማለት ነው። “ሳባ” የመን እንጂ “ኢትዮጵያ” እንዳይደለች አፄ ዘርአ ያዕቆብን ምስክር ልጥራ። አትቀየሙትና እንዲህ ይላል፤
ሰላም እብል ለካሌብ መነኮስ፤ (ለመንኵሴው ለካሌብ ሰላምታ አቀርባለሁ)
እመንገለ ክብሩ ንጉሥ፤ (በክብሩ በኩል ንጉሥ ነው)
ይሜርድ ባሕረ ከመ እንተ የብስ፤ (በባሕር ላይ እንደ በምድር ላይ ይነጕዳል)
ብሔረ ሳባ በጺሖ፤ (ሳባ ሀገር ደርሶ)
ለአይሁዳዊ ነጽሖ፤(አይሁዳዊውን ወቃው)
ወበውስቴቱ ሐነጾ ለአምካክ ጽርሖ። (በዚያ ውስጥም ለአምላክ አዳራሹን ሠራለት)
አንድ አይሁዳዊ ንጉሥ ናግራን ከተማ ያሉትን ክርስቲያኖች ሲያሠቃይ፥ ንጉሥ ካሌብ ባሕር ተሻግሮ የመን ድረስ ዘምቶ ስላዳናቸው፥ ንጉሥ ዘርአ ያዕቆብ የተቀኘለት ነው፤ ቅኔው ነግሥ ይባላል።
ባለፈው ጽሑፌ እንደመዘገብኩት፥ “ዓላማ ዘዴን ያጸድቀዋል” እንዲሉ፥ “ዶክተር ፍቅሬ ቶሎሳ ጂግሳ ዓላማው አማሮችና ኦሮሞች በአንድ ሀገር ውስጥ በወንድማማችነትና በሰላም እንዲኖሩ ምክንያት ለመስጠት ስለሆነ በምንም ዘዴ (ዋሽቶም ቢሆን) ቢጠቀም ክፋት አናይበትም” የሚሉ አሉ። እንዳፋቸው ያድርግላቸው። ግን ይህ የሐሰት ታሪክ የኢትዮጵያ አንድነት በሚያንሰፈስፋቸው ኢትዮጵያውያን ስሜት ከመቀለድና ከመጠቀም አልፎ በክልልና በጎሳ ፖለቲካ የሚያምን አንድ የኦነግ ሰው ነፍስ አይማርክም። የተረቱ ሰለባ የሆኑት የአንድነት ተስፋ የናፈቃቸው ምስኪናን አንድነቶች ብቻ ናቸው።
በመጨረሻም፥ ከሌሎች በላይ ነኝ ትላለህ ያላችሁኝ ሌሎች ሲያከብሩን፥ የትምህርት ተቋማት ሲሸልሙን ሰምታችሁ ይሆናል እንጂ፥ እኔማ እነሆ፥ ሌሎቹ ሲንቋችሁ፥ ከናንተ እኩል ሆኜ እወያያችኋለሁ። መልካም ገና።