ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ዓለም ዐቀፉ የሰብኣዊ መብት ተሟጋቹ ድርጅት፣ አምንስቲ ኢንተርናሽናል ያወጣውን መግለጫ የኢትዮጵያ መንግሥት ውድቅ አደረገ።
አምነስቲ ዓርብ ዕለት ባወጣው ዝርዝር ሪፖርት የኤርትራ ወታደሮች በአክሱም ከተማ የፈጸሙት ግድያ በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል ሳይሆን አይቀርም የሚል ግምታዊ አስተያየት የሰፈረበት መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል።
ጉዳዮን አስመልክቶ ማብራሪያ የሰጠው የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ፤ በአነስቲት የወጣው ሪፖርት ባልተሟላ መረጃና ውስን በሆነ የጥናት ዘዴ ተዘጋጅቶ የቀረበ ነው ከማለቱ ባሻገር፤ ለሪፖርቱ ግብአትነት ጥቅም ላይ የዋሉት መረጃዎች በምሥራቃዊ ሱዳን ከሚገኙ ስደተኞችና አክሱም ውስጥ ካሉ ግለሰቦች በስልክ የተሰበሰበ ቁንጽል መረጃ ነው ሲል ተችቷል።
በምስክርነት ከተሳተፉትከስደተኞች መካከልም አንዳንዶቹ የህወሓት የቀድሞ ተዋጊዎች የነበሩ መሆናቸውንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አጋልጧል።
ኤርትራም በተመሳሳይ የአምነስቲን ሪፖርት እንደማትቀበል የሀገሪቱ የማስታወቂያ ሚኒስትር አቶ የማነ ገብረ መስቀል በትዊተር ገጻቸው አስታውቀዋል። ሪፖርቱ በአብዛኛው የተንጠላጠለው ሱዳን መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ያሉ 31 ግለሰቦች ላይ እንደሆነም ባለ ሥልጣኑ ጠቁመዋል።
በመጠለያ ውስጥ ያሉት አብዛኞቹ በመቶዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን በተገደሉበት የማይካድራው ጭፍጨፋ ተሳታፊ ሆነው የሸሹ የህወሓት ሚሊሻዎች መሆናቸውንም የኤርትራው ሚኒስትር ገልጸዋል።