ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– አቶ ልደቱ አያሌው ከፖለቲካው ዓለም በገዛ ፈቃዳቸው ራሳቸውን እንዳገለሉ ይፋ አድርገዋል።
ይሁንና እዚህ ውሳሌ ላይ ለመድረስ “ገፊ ምክንያት ሆነውኛል” ያሏቸው ሀሳቦች እርስ በርሳቸው የሚጣረሱ ስለመሆናቸው አየተወሳ ይገኛል።
አቶ ልደቱ ከፖለቲከኝነት መገለላቸውን ይፋ ባደረጉበት መልዕክታቸው “…በጤናዬ ላይ የተሰጠኝ የሀኪም ምክር እና ትዕዛዝ እንዲሁም የሀገሪቱ አጠቃላይ የፖለቲካ ሁኔታ ለተሳትፎ የሚጋብዝና አበረታች ባለመሆኑ፤ በተለይም የገዥው ፓርቲና መንግስት አፋኝነት እና ከፍተኛ የአምባገነንነት መንፈስ መላበስ የሚጠበቀውን ለውጥ ለሀገሪቱ የማያመጣ ከመሆኑ ባሻገር ለመግባባት ፍላጎት የሌለው በመሆኑ ከፖለቲካ ለመሰናበት ምክንያት ሆኖኛል። …በህይወት ለመቆየትም የግድ ይህንን ውሳኔ መወሰን አለብኝ” ብለዋል።
የአቶ ልደቱን ውሳኔና ያስተላለፉትን መልዕክ ተከትሎ በርካታ ሀሳብና አስተያየቶች እየተሰነዘረ ሲሆን፣ ከነዚህም ውስጥ “የአቶ ልደቱ አያሌው ስንብት በፖለቲካ ክስረት ወይስ በጤና ችግር?” የሚለው በስፋት እየተንሸራሸረ ይገኛል።
አቶ ልደቱ ከ97 ምርጫ ውጤት መጭበርበር ጋር ተያይዞ የሀገሪቱ ታዋቂ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ለእስር ሲዳረጉ እርሳቸው ፓርላማ መግባታቸው በብዙሃን ኢትዮጵያውያን ዘንድ እምነት እንዳሳጣቸው ይታወቃል።