ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም በትግራይ ለተፈጠረው ችግር ኃላፊነቱን የሚወስደው የህወሃት ቡድን እንደሆነ ለድርጅቱ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በጻፈው ማስታወሻ መግለጹን ይፋ አድርጓል።
ሚስጥራዊ ነው የተባለውን የውስጥ ለውስጥ ማስታወሻ እንዳገኘው የገለጸው ፎሪን ፖሊሲ መጽሔት ነው።
መጽሄቱ እንዳብራራው፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ኃላፊ አቺም ስቴይነር በምስራቅ አፍሪካ ደም አፋሳሽ ግጭት እንዲፈጠር ያደረገው ኢትዮጵያን ላለፉት 27 አመታት የመራው የህወሃት አመራር በትግራይ ክልል በሚገኘው የሰሜን እዙ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት በመፈጸምና እዙን ለመቆጣጠር ያለመ እንደሆነ ገልጿል፡፡
የህወሃት ድርጊት የጦርነት ቅስቀሳ ስለመሆኑ በምስጢራዊው ሰነድ መገለጹን የጠቀሰው መጽሄቱ፣ “ድርጊቱ በየትኛውም አገር ወታደራዊ አጸፋ የሚያሰጥ ድርጊት መሆኑን አስረድቷል” ብሏል፡፡ ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ባለፉት ሁለት ዓመታት ለህወሃት ቡድን ትንኮሳ ትኩረት ሳይሰጥ መቆየቱንና ቡድኑ ከመንግስት ጋር ድርድር ለማድረግ ፍቃደኛ ሳይሆን መቅረቱ መገለጹንም አመልክቷል፡፡
ለጋሽ ድርጅቶች የኢትዮጵያ መንግስትን በተለይ በግጭቱ ወቅት ተፈጽመዋል ለተባሉት የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ላይ ብቻ ትኩረት ከማድረግ ይልቅ በልማትና በሰብአዊ ድጋፎች ላይ ትኩረት ቢያደርጉ መልካም እንደሚሆን በሰነዱ ላይ መጠቀሱን አያይዞ የጠቀሰው ፎሪን ፖሊሲ መጽሔት፣ በትግራይ ተፈጽሟል የተባለው የሰብአዊ መብት ጥሰት ላይ የሚደረገው ምርመራ የዓለም አቀፍ ተቋማት ተሳትፎ ሊኖርበት እንደሚገባና በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን መመራት እንዳለበትም ምክረ ሀሳብ መቅረቡን እንዲሁም የህወሃት ቡድን ከአላማጣ ከተማ 10,000 ታራሚዎችን በመልቀቅ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አካባቢውን በስርዓት እንዳያስተዳድር እንቅፋት ስለመፍጠሩ በሰነዱ መገለጹን አስታውቋል፡፡