ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም፣ የትግራይ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት የነበሩት ወ/ሮ ሕርቲ ምህረተአብ እና የክልሉ መንግስት አማካሪ የነበሩት ወልደጊዮርጊስ ደስታ፣ እንዲሁም በእነ አባይ ወልዱ የክስ መዝገብ ላይ ከሚገኙ ተከሳሾች ውስጥ አምደማርያም ተፈራ በ30 ሺ ብር ዋስ እንዲለቀቁ ወስኗል፡፡
ይሁንና ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም በትግራይ ክልል ባለው ኮማንድ ፖስት የሚጣራ ጉዳይ በመኖሩ ቀዳሚ ምርመራ እስኪሰማ ድረስ በወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርዓት ሕግ አንቀጽ 28 መሰረት በዋስ እንዲለቀቁ መወሰኑ “የፍትሕ ስርዓቱ ዛሬም ነፃና ሚዛናዊ ላለመሆኑ ማሳያ ነው በሚል” ሰፊ ተቃውሞ አስነስቷል፡፡
በማህበራዊ ሚዲያዎች ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተከታዮች ያሏቸውና በመንግስት ደጋፊነት የሚታወቁ ሰዎች ጭምር በወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም ላይ የተሰጠውን ውሳኔ እየተቃወሙ ነው።
በተለይ አቶ ስዩም ተሾመ “እንሆ ዛሬ #ፍትህ የሚባል ነገር ሞቶ ተቀብሯል። የወይዘሮ ኬሪያ መፈታት የሚያሳየው የኢትዮጵያን ልጆች በግፍ መገደላቸው፣ ቀባሪ አጥተው የአሞራና ጅብ ሲሳይ መሆናቸው ትክክል እና አግባብ ነው። ይህን ከማየት ዓይኔ ቢጠፋ እመርጣለሁ‼️ ይህ እውን ከሚሆን ኢትዮጵያዊነቴን መካድ ይቀለኛል። ይህን ከመስማት ሞትን እመርጣለሁ” በማለት መራር ተቃውሞውን አሰምቷል።