በአዲስ አበባ የታክሲዎች አድማ ተሳፋሪዎች ሲንገላቱ ዋሉ!

በአዲስ አበባ የታክሲዎች አድማ ተሳፋሪዎች ሲንገላቱ ዋሉ!

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– በአዲስ አበባ የሚኒባስ ታክሲ አሽከርካሪዎችና ባለንብረቶች ከነዳጅ ዋጋ መጨመርና አጋጠመን ካሉት የተጋነነ ቅጣት ጋር በተያያዘ ላነሷቸው ጥያቄዎች “የሚመለከተው አካል ተገቢ ምላሽ አልሰጠንም” በሚል ዛሬ የስራ ማቆም አድማ አደርገዋል። በዚህም ትራንስፖርት ተጠቃሚው ህብረተሰብ ለከፍተኛ እንግልት ተዳርጎ መዋሉ ተስተውሏል።

የሚኒባስ ታክሲ አሽከርካሪዎችና ባለንብረቶቹ ከቀናት በፊት ጀምሮ “የነዳጅ ዋጋውና የተተመነልን ታሪፍ ተመጣጣኝ አይደሉም። በትራንስፖርት ተቆጣጣሪዎች እየተጣለብን ያለው ቅጣትም የተጋነነ ነው” በሚል መንግስት አፋጣኝ የመፍትሄ ምላሽ እንዲሰጣቸው ሲጠይቁ የቆዩ ሲሆን፣ ዛሬ አድማ ለማድረግ የተነሱትም ጥያቄአቸው ምላሽ በመነፈጉ እንደሆነ ገልፀዋል።

ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ በበኩሉ አድማውን በሚመለከት በኃላፊ ኢንጂነር ስጦታው አከለ በኩል በሰጠው ምላሽ “የተወሰኑ ባለታክሲዎች ዛሬ ወደ ስራ እንዳልገቡ እናውቃለን፡፡ የታክሲ ባለቤቶች ታሪፍ እንዲሻሻልላቸው ጠይቀውናል፤ በዚህም የህዝብን የመክፈል አቅም እና የነዳጅ ዋጋን ታሳቢ ያደረገ ማሻሻያ ተደርጓል” ብለዋል።

ኃላፊው አያይዘውም “ይሁንና ከላይ ከተቀመጡት ምክንያቶች ውጭ ዝም ብለን የታሪፍ ማሻሻያ አናደርግም። በዛሬው አድማ ላይ በተሳተፉት ላይም እርምጃ እንወስዳለን” ሲሉ ተናግረዋል።

በአድማው የተሳተፉት “ጥቂት ታክሲዋች ናቸው” የሚሉት ኃላፊው፣ በከተማው የትራንስፖርት ችግር እንዳይፈጠር ፐብሊክ ባስ፣ ሸገር ባስ እና ድጋፍ ሰጪ አውቶቡሶችን በስፋት የመጠቀም አማራጭ መከተላቸውንም ተናግረዋል።
ዛሬ በርካታ የከተማዋ ነዋሪ ተሳፋሪዎች በታክሲ እጦት ሲንገላቱና ከወትሮው የተለዩ ረጃጅም ሰልፎች መኖራቸውን ዘጋቢያችን በተለያዩ አካባቢዎች ተዘዋውሮ ለመመልከት ችሏል፡፡

LEAVE A REPLY