በህዳሴ ግድብ ጉዳይ:- አሜሪካ በ3ቱም ካልተጋበዘች ጣልቃ እንደማትገባ አስታወቀች!

በህዳሴ ግድብ ጉዳይ:- አሜሪካ በ3ቱም ካልተጋበዘች ጣልቃ እንደማትገባ አስታወቀች!

ኢትዮጵያ የቀደመ አቋሟን አፀናች!
“ሱዳን ወደ 2ኛ አማራጭ ተሻገረች!”


ኢትዮጵያ ነገ ዜና
– አሜሪካ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ በሚደረገው ድርድር ሶስቱም ሀገራት ካልጋበዟት በስተቀር ጣልቃ እንደማትገባ አስታውቃለች።

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የቀጠናዊ ጉዳዮች ቃል አቀባይ ሳሙኤል ዋርበርግ “ቴን” በተባለ የግብጽ የሳተላይት ቴሌቪዥን ላይ በሚሰራጨው “ፔን ኤንድ ፔፐር” ዝግጅት ላይ በዙም ተጋብዘው በሰጡት ማብራሪያ “የአባይ ወንዝ ለግብጽ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያም ለሱዳንም በጣም ጠቃሚ ወንዝ መሆኑን አሜሪካ ታምናለች” ብለዋል።

በአገራቱ መካከል ያለው ልዩነት በውይይትና በድርድር እንዲፈታ አገራቸው ድጋፍ ማድረጓንና አሜሪካ በግድቡ ዙሪያ ያሉ አለመግባባቶች መፍታት ያለባቸው በሶስቱ አገራት ብቻ ነው የሚል አቋም እንዳላት የገለጹት ቃል አቀባዩ፣ አሜሪካ ሶስቱም አገራት ጥሪ ካደረጉላት ብቻ የሚጠበቅባትን አዎንታዊ ሚና ለመወጣት ዝግጁ መሆኗን አመልክተዋል።

በተያያዘ፣ ግድቡ የሚገኝበትን ወቅታዊ ሁኔታና የግድቡን 10ኛ ዓመት የተመለከተ ሲምፖዚየም ትናንት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ያካሄደ ተካሒዷል።

በሲምፖዚየሙ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ኢንጂነር ዶ/ር ስለሺ በቀለ የህዳሴው ግድብ አጠቃላይ ግንባታ 79% እንደደረሰ ገልፀው፣ “በቀጣዩ ክረምት ቀጠሮ የተያዘለት 2ኛው ዙር የውሃ ሙሌት በምንም ዓይነት መልኩ አይራዘምም፤ ለዚያ የሚያበቃ አሰራርና ምክንያትም የለም” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ሲምፖዚየሙን በንግግር የከፈቱት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሄራዊ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ደመቀ መኮንን በበኩላቸው “ዓባይን ማልማትና የህዳሴ ግድቡን ማጠናቀቅ ለነገው ትውልድ ከመስራት በላይ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ማረጋገጥ ጭምር ነው” ብለዋል።

በሌላ በኩል፣ ሱዳን ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ወደ ሁለተኛ አማራጭ እየተሸጋገረች መሆኑን ሱዳናዊው የፖለቲካ ተንታኝ ኦስማን ማርጋኒ ተናገሩ።

ኦስማን ማርጋኒ ትናንት በስካይ ኒውስ ቀርበው “ካርቱም አሁን ላይ በግድቡ ግንባታ እና የድርድር ሂደቱ ላይ የአዲስ አበባን የቆየ እና የማይለዋወጥ አቋም እንደምትረዳ ተስፋ አድርጋለሁ” ብለዋል።

“ኢትዮጵያ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የአውሮፓ ህብረት፣ የአፍሪካ ሕብረት እና አሜሪካ በአደራዳሪነት ይግቡ የሚለውን ሀሳብ ውድቅ ካደረገች በኋላ ሱዳን አዲስ የዲፕሎማሲ ዘዴን ትጠቀም ይሆን?” በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ “እኔ አይመስለኝም” የሚል መልስ ሰጥተዋል ፤ ለዚህም ምክንያት “ካርቱም የጥንቃቄ እርምጃዎችን ጀምራለች” የሚል ነው፡፡
በዚህም አማራጭ ሱዳን የውሃ ብክነትን ለማካካስ የጥንቃቄ እርምጃዎችን መውሰድ እና ውሃ ቀድማ የመያዝ እቅድ እንደምትከተልም የፖለቲካ ተንታኝ ኦስማን ማርጋኒ አስታውቀዋል።

LEAVE A REPLY