ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት ዛሬ ባስተላለፈው መልዕክት፣ መንግስት ከአጥፊው የህወሓት ቡድን ጋር ለተባበሩ አካላት የመጨረሻ ጥሪ ማቅረቡ ተመልክቷል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ከሕገ ወጡ የሕወሐት ቡድን ጋር ለተባበሩ አካላት ከመንግሥት የተሰጠ የመጨረሻ ማሳሰቢያ በሚል ዛሬ ባወጣው ጥሪ
“ሕገ ወጥ ጥቃቱ እና ተያያዥ በሆኑ የወንጀል ተግባራት ጉልህ ተሳትፎ አላቸው ተብለው ከተጠረጠሩ እና በዚህም መነሻ የፍርድ ቤት መያዣ ከወጣባቸው ከፍተኛ የሕወሐት ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ አመራሮች በስተቀር ሌሎች ዜጎች ያለ ሥጋት ወደ ቀደመው ሰላማዊ ኑሯቸው እንዲመለሱ” ሲል ጥሪ አቅርቧል።
አያይዞም “እነዚህ ወገኖች በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ወደ ቀያቸው እና መኖሪያቸው በመመለስ ማኅበረሰቡን እንዲቀላቀሉ፤ በዚህ መንገድ ከአጥፊው ቡድን ተለይተው ወደሰላማዊ ኑሯቸው የሚመለሱ የክልሉ ተወላጅ ዜጎች፣ የትኛውም የሕግ ተጠያቂነት ሳይኖርባቸው፣ ከአጥፊ ተግባራት ተቆጥበው፣ ወደ ሥራቸው እና ኑሯቸው በሰላም መሠማራት ይችላሉ” ብሏል።
“እነዚህን ዜጎች በመልካም ሁኔታ በመቀበል እንዲተባበሩ እና የተቻላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው ለየሚመለከታቸው የጸጥታ፣ የአስተዳደር እና የሕግ አስከባሪ ተቋማት አስፈላጊው መመሪያ ተሰጥቷቸዋል” ያለው የመንግስት የመጨረሻ ማሳሰቢያው፤ የጥፋት ቡድኑ አካል ሆነው በተፈጸመው ወንጀል ከፍተኛ ድርሻ አላቸው ተብለው የተጠረጠሩ፣ የፍርድ ቤት መያዣም የወጣባቸው ከፍተኛ የሕወሓት ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ አመራሮች፣ በሰላም እጃቸውን ለሕግ አስባሪ ተቋማት እንዲሰጡ ጥሪ አቅርቧል።
“እነዚህ አመራሮች እስከዛሬ ከደረሰው ሀገራዊ ጥፋት እና ጉዳት በመማር፣ ለፍትሕ ራሳቸውን በማቅረብ፣ ተጨማሪ ሀገራዊ ኪሣራ እንዳይደርስ እና በከንቱ የዜጎች ደም እንዳይፈስ የበኩላቸውን በጎ አስተዋጽዖ እንዲያደርጉ መንግሥት ጥሪ ያቀርባል።
ይሄንን የሚያደርጉ ከፍተኛ የሕወሐት ወታደራዊና ፖለቲካዊ አመራሮች ራሳቸውን ከከፋ ቅጣት፣ ወገናቸውን ከመጎሳቆል ይታደጉታል፤ ይሄንን የመጨረሻ ጥሪ ተጠቅመው ራሳቸውን ለፍትሕ በማያቀርቡ የሕወሐት ከፍተኛ ወታደራዊና ፖለቲካዊ አመራሮች ላይ ግን፣ ሕግ በሚፈቅደው ሁሉም ዓይነት መንገድ ሕግ ለማስከበር ሲባል አስፈላጊው ሁሉ የሚፈጸም መሆኑን ቀድመን እንገልጻለን” ሲልም የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል።