ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– እስከ ዛሬ ድረስ 2000 ሰዎች የኮቪድ -19 ክትባት የወሰዱ ሲሆን፣ 35 ያህል ሰዎች ላይ የጎንዮሽ ጉዳት መታየቱ ሪፖርት ተረጋግጧል።
ክትባቱ የበሽታውን ስርጭት ለመግታት የሚያግዝ በመሆኑ በጎንዮሽ ጉዳቱ መደናገጥ እንደማያስፈልግ የገለፀው የኢትዮጵያ ምግብ እና መድሀኒት ቁጥጥር ባለስልጣን በበኩሉ፣ በኢትዮጵያ እየተሰጠ ያለው የኮቪድ-19 ክትባት የፈቃዱን የአፈፃፀም መመሪያ መስፈርት ያሟላ መሆኑን ገልጾ፣ የክትባቱን ደህንነት ለመከታተል እና በሚፈለገው ፍጥነት አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል የቁጥጥር ስርዓት መዘርጋቱን አስታውቋል።
በተያያዘ፣ የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ትናንት ባወጣው መግለጫ “የአስትራዜኒካ ክትባትን መከተብ ደህንነቱ የተረጋገጠ ነው” ብሏል።
ክትባቱ የጤና እክል ያስከትላል በሚል በ13 የአውሮፓ ሀገራት እንዲታገግ ተደርጎ እንደነበር የጠቀሰው የአውሮፓ ህብረት የህክምና ኤጀንሲ፣ በክትባቱ ምክንያት “የደም መርጋት ማጋጠሙን ተከትሎ ምርመራ አድርጊያለሁ” ብሏል።
“በምርመራው ውጤት መሰረት ክትባቱ ከደም መርጋት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንደሌለው አረጋግጫለሁ። ክትባቱ ዜጎችን ከኮቪድ 19 ለመጠበቅ የሚያስችል በመሆኑ ይህንን ማጣራት ተከትሎ የአውሮፓ ሀገራት በቅርቡ ክትባቱን ማሰራጨታቸውን ይቀጥላሉ” ሲልም አስታውቋል።