ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በሰሜን ሸዋ ዞን አጣዬ አካባቢ የተከሰተው የጸጥታ ችግር፣ አንዱ ጋር “ጋብ ብሏል” ሲባል ሌላው ጋር ተፋፍሞ እየቀጠለ በአካባቢው ያለው ውጥረት አሁንም አለመብረዱና የሟቾች ቁጥርም እያሻቀበ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል።
ለኢትዮጵያ ነገ በስልክ የተናገሩ የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚገልፁት፣ በተለይ ከቀናት በፊት ጥቃቱ የተጀመረባት የአጣዬ ከተማ ከትናንት በስቲያ (መጋቢት 11/2013 ዓ.ም) ምሽቱን ተኩስ ሳይሰማባት ብታድርም ከትናንት (መጋቢት12/2013 ዓ.ም) ከንጋት 11፡00 ጀምሮ ግን ጠንከር ያለ ውጊያ እየተካሄደባት ነው ብለዋል።
በግለሰቦች እጅ ሊያዙ የማይችሉ ከባድ የጦር መሳሪያዎች ጭምር ወደ ነዋሪው እየተተኮሱ በመሆኑንም በሰውና በንብረት ላይ ከባድ ጉዳት እየደረሰ ይገኛል።
እስካሁን ባለው መረጃ ግጭቱ በተከሰተባቸው አጣዬ፣ ካራቆሬ፣ ማጀቴ፣ ሰንበቴ፣ ጀዋሀ፣ ጅሌ ጥሙጋና ዙጢ ከፍተኛ መጠን ያለው ንብረት መዘረፉን፣ ቤት መቃጠሉን፣ የበርካታ ሰዎች ሕይወት መጥፋቱን ለማወቅ ሲቻል፣ የአጣዬ ከተማ ነዋሪዎችም በአቅራቢያ ወደሚገኙ የገጠር ቀበሌዎች እየሸሹ መሆኑን ተመልክቷል።
“መጋቢት 11/2013 ዓ.ም ግጭቱ ወዳለባቸው ስፍራዎች የገባው የመንግሥት የጸጥታ ኃይል፣ ውጥረቱን ለማርገብ ጥረት እያደረገ መሆኑ ቢነገርም፣ ችግሩ ግን እንደቀጠለ ነው” በማለት የገለፁ የአካባቢው ነዋሪዎች፣ ጥቃት ፈፃሚው “የተደራጀ ቡድን” የመንግስት ፀጥታ ኃይሎችን አሰላለፍ እያየ የጥቃት አቅጣጫውን እንደሚቀያይርና ትናንት ማለዳም ማጀቴ ከተማን ወደመክበብ በመሻገሩ የከተማዋ ነዋሪ በተፈጠረበት ስጋት ከተማውን ለቆ እየወጣ መሆኑን አስታውቀዋል።
“ሽብር ፈጣሪዎቹ የተደራጁና ከባድ መሳሪያ የታጠቁ በመሆኑ በአካባቢው ከተሰማራው የፀጥታ ኃይል አንፃር የኃይል አለመመጣጠን ይስተዋላል” የሚሉት እነዚሁ የአካባቢው ነዋሪዎች፣ የነዋሪው ስጋት እየጨመረ በመምጣቱ ዛሬ ግጭቱ ባልተከሰተባት በሸዋሮቢት ከተማ ጭምር ሱቆች፣ ሆቴሎች እና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ዝግ ሆነው መዋላቸውንም ተናግረዋል።
ከተለያየ አቅጣጫ የሚደርሱን በርካታ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ ውጥረቱ አድማሱን እያሰፋ ሲሆን፣ ከሚሴ አካባቢ ዛሬም ውጥረት መኖሩንና በተለያዩ አቅጣጫዎች የተኩስ ልውውጥ እንዳለ ለመረዳት ተችሏል።
ይሁንና የአማራ ክልል መንግስትና የክልሉ ፀጥታ ሃላፊዎች በሰጧቸው መግለጫዎች ውጥረት በተከሰተባቸው አካባቢዎች የክልሉና የፌደራል ፀጥታ ኃይሎች ሰላም የማረጋጋት ተልዕኳቸውን በብቃት እየተወጡ መሆናቸውን ገልፀው፣ በአጣየና በአካባቢው የተፈጸመውን ዝርዝር ጥቃት፣ የደረሰውን ሰብዓዊና የንብረት ጉዳት በፍጥነት አጣርተው መረጃውን ለሕዝቡ ይፋ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል፡፡