“የሱዳን ወታደራዊ ክንፍ ለሶስተኛ ወገን ጥቅም እየሰራ ነው” የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

“የሱዳን ወታደራዊ ክንፍ ለሶስተኛ ወገን ጥቅም እየሰራ ነው” የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በፖለቲካ፣ በምጣኔ ሀብትና በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ወቅታዊ አበይት ክንውኖች ላይ ያተኮረውን ሣምንታዊ መግለጫ በሰጡበት ወቅት “የሱዳን ወታደራዊ ክንፍ የሱዳንን ሕዝብ ፍላጎት በተቃረነ መልኩ ለሶስተኛ ወገን ጥቅም እየሰራ ነው ሲሉ” ገለፁ።

አምባሳደር ዲና በዚሁ ሳምንታዊ መግለጫቸው፣ በፖለቲካ ዲፕሎማሲ መስክ የአፍሪካ ኅብረት የሠላም ጥበቃ ምክር ቤት የቨርቹዋል ውይይት፣ የአሜሪካ መንግስት ሴናተር ክሪስ ኩንስ የኢትዮጵያ ቆይታና ሌሎች ሁነቶችን ለአብነት አንስተዋል።

የአሜሪካው ሴናተር ኩንስ በቆይታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፣ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንና ከሠብዓዊ መብት ኮሚሽን ሃላፊ ጋር እንደተወያዩ የገለፁት ቃል አቀባዩ፣ በውይይታቸውም በሰሜን ኢትዮጵያ በተደረገው የሕግ ማስከበር መነሻና አሁናዊ ሁኔታ፣ የሠብዓዊ መብትና ሠብዓዊ እርዳታ አቅርቦትና በኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር እንዲሁም በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ውጤታማ ውይይት ስለማካሄዳቸው ተናግረዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድርን በተመለከተ የድርድሩ መሪ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀ መንበርነት ከደቡብ አፍሪካ ወደ ኮንጎ መዛወሩን ተከትሎ በሂደት ላይ እንደሆነ የጠቆሙት አምባሳደር ዲና፣ በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ጉዳይ አቋሟን የምትቀያይረው ሱዳን በዋናነት የግድቡ ጥራትና መረጃ መለዋወጥ ላይ ሁለት ጥያቄዎች እንደምታነሳም ጠቁመዋል።
“ይህ ሆኖ እያለ ግን የሱዳን ወታደራዊ ክንፍ ከሱዳን ሕዝብ ፍላጎት በተቃርኖ በመቆም ለሶስተኛ ወገን ጥቅም እየሰራ ነው” በማለትም አስታውቀዋል።

LEAVE A REPLY