በፓርላማ የቀረቡ ጥያቄዎች የምክር ቤቱን የሥነ-ምግባር ደንብ የጣሱ ናቸው” ተባለ 

በፓርላማ የቀረቡ ጥያቄዎች የምክር ቤቱን የሥነ-ምግባር ደንብ የጣሱ ናቸው” ተባለ 

ኢትዮጵያ ነገ ዜናጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መጋቢት 14/2013 ዓ.ም በተካሄደው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ከአንዳንድ የምክር ቤቱ አባላት የተነሱ ጥያቄዎች “የምክር ቤቱን የአባላት ሥነ-ምግባር ደንቦች የጣሱ ናቸው” በሚል ተቃውሞ እየቀረበባቸው ሲሆን፣ የአማራ ልዩ ሀይልን በሚመለከት የቀረቡ ጥያቄዎችም የውዝግብ መነሻ መሆናቸው ተመልክቷል።

“በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚቀርቡ ጥያቄዎች፣ በአባላት ሥነ-ምግባርና ደንብ አሰራሩ መሰረት ስብሰባው ከመካሄዱ ከ3-5 ባሉት ቀናት ውስጥ በጽሁፍ ገቢ መሆን አለባቸው” የሚል መመሪያ መኖሩን ያወሱ አስተያየት ሰጪዎች፣ “ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚቀርቡ ጥያቄዎችን በየአጀንዳው ለይቶና አደራጅቶ ወደ ጠ/ሚ/ጽ/ቤት የሚልከው አፈ-ጉባዔ ጽ/ቤት ቢሆንም፣ የጥያቄዎቹን ይዘት ከፖለቲካ፣ ከሕግ፣ ከሞራል፣ ወዘተ አኳያ የሚገመግመው “አስተባባሪ ኮሚቴ” የሚባለው ቡድን ነው። አስተባባሪ ኮሚቴ የሚባለው ስብስብ፣ በቀድሞው ኢህአዴግ የአራቱ ብሔራዊ ድርጅቶች የመሰረታዊ ድርጅት ተጠሪዎች የሚገኙበት ሲሆን፤ ሰብሳቢያቸው በፓርላማ የመንግሥት ተጠሪ ተብሎ የሚመደበው አካል ነው። በአሁኑ ወቅት የኦሮሞ ብልጽግና ወኪል አቶ ጫላ ለሚ የአስተባባሪ ኮሚቴው ሰብሳቢ ነው።

በቀደመው አሰራር የአስተባባሪ ኮሚቴው ዋና ተልዕኮ ከፓርቲው ፍላጎትና አቋም ውጭ አባላቱ እንዳያፈነግጡ ጠርንፎ መያዝ ነው። አስተባባሪ ኮሚቴው ከፓርላማው አመራር ጋር ሆኖ ጥያቄዎቹን ፈትሾና ገምግሞ ከስብሰባው ሦስት ቀናት በፊት ወደ ጠ/ሚ/ጽ/ቤት የሚልክ ቢሆንም፤ በአሁኑ የምክር ቤቱ ውሎ ስብሰባ ግን የኦሮሞ ብልጽግና ካወጣው መግለጫ ጋር የሚናበብና ከሃያ አራት ሰዓት ወዲህ የተከሰቱ ክስተቶች ጨምሮ በተዛባና አደገኛ በሆነ የፖለቲካ አተያይ ከሁለት የም/ቤቱ አባላት ጥያቄዎች ሲቀርቡ ተመልክተናል” በማለት የአሰራር ደምብ ጥሰት መፈፀሙን አመልክተዋል።

“ምክር ቤቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገኙበት በመደበኛም ሆነ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ሲመክር ጥያቄዎቹ ቀድመው የገቡ ቢሆን እንኳ፣ ማሻሻያ ለማድረግ ወይንም አንገብጋቢ ጥያቄዎችን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ማቅረብ ቢያስፈልግ ለአስተባባሪ ኮሚቴው ድጋሚ ማቅረብ የግድ ይላል።

ይህ የሚሆነው ከፖለቲካ ጥርነፋው ባሻገር በሃይማኖትም ይሁን በብሔር ሕዝብን በሕዝብ ላይ የሚያነሳሱ፣ ጥላቻንና ግጭትን የሚያባብሱ፣ የፌዴሬሽኑን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥሉ፣ ወዘተ ጥያቄዎች በድንገት እንዳይቀርቡና ችግሮች እንዳይፈጠሩ በሚል ነው። ከትናንት በስቲያ የሆነው ግን በተቃራኒው ነው” ሲሉ አያይዘው የገለፁት እነዚሁ ታዛቢዎች፣ “ማክሰኞ ዕለት በነበረው የፓርላማ ውሎ፣ በአማራ ክልል የከሚሴ ልዩ ዞን የምርጫ ወረዳዎች የፓርላማ ተመራጭ የሆኑ ሁለት የምክር ቤት አባላት ያቀረቡት ጥያቄ፣ በይዘት ደረጃ የምክር ቤቱን የአባላት ሥነ-ምግባርና ደንብ የሚቃረን፣ በክልሉ ውስጥ ሃይማኖታዊ መካረሮችን የሚያባብስ፣ የሥልጠናና ሎጀስቲክስ ድጋፍ ያለውን አሸባሪ ታጣቂ ኃይልን ውድመት የሚክድ፣ የአማራ ክልልን መንግሥት፣ የፖለቲካ አመራሩንና የክልሉን ልዩ ኃይል ገጽታና እውነተኛ ማንነት የማይገለጽ ስም ማጥፋትና ጥላቻ የታየበት ሆኖ ተገኝቷል።

በተለይም የክልሉን ልዩ ኃይል ‘የጦር ወንጀል ፈጽሟል’ በሚል ከአንደኛው የምክር ቤት አባል የቀረበው ስም ማጥፋት በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ስም አጥፊውን ብቻ ሳይሆን የምክር ቤቱን አስተባባሪና የፓርላማ አመራሩን በአሰራር ደረጃ ያስጠይቃል” ሲሉ መረር ያላ አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል።

በተያያዘ፣ “የኢትዮጵያ መከታ የሆነውን የአማራ ልዩ ሀይልን ያልተገባ ስም የሚሰጡ አካላት ከድርጊታቸው እንዲታረሙ” በማለት የአማራ ክልል ሰላምና ደህንነት ቢሮ ሀላፊ አቶ ሲሳይ ዳምጤ አሳስበዋል።

አቶ ሲሳይ በዚሁ መግለጫቸው፣ “የአማራ ልዩ ሀይል የክልሉን ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ እየሰራ ያለውን ስራ በእጅጉ አድንቀው፤ ልዩ ሃይሉ ምንም እንኳን የአማራ ስም ቢሰጠውም በክልሉ ውስጥ ለሚገኙ ማንኛውም ነዋሪ ሰላም መረጋገጥ እየሰራ ያለ ኢትዮጵያዊ ስብዕናን የተላበሰ ነው፤ ይህን ሃይል ያልተገባ ስም የሚሰጡ አካላት ከድርጊታቸው እንዲታረሙ” ሲሉም አስጠንቅዋል።

“የአማራ ክልል ልዩ ኃይል ስሙ የአማራ ይሁን እንጂ ግብሩ ኢትዮጵያዊ ነው” በማለት በፓርላማ የተነሱትን ጥያቄዎች የተቃወሙት ደግሞ የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ ባይነሳኝ ዘሪሁን ናቸው።

“የአማራ ልዩ ኃይል ሊሸለምና ሊሞገስ እንጂ ኢትዮጵያን ለማዳን የፈሰሰ ደሙ ሳይደርቅና ቁስሉ ሳይጠግ ስም ማጥፋት ኢትዮጵያን ለማሳነስ ከሚተወኑ የሀሰት ተውኔቶች አንዱ እንደሆነ እንረዳለን” በማለትም ሀሳባቸውን ሰንዝረዋል።

እንደዚሁም፣ “የአማራ ልዩ ኃይልን በተሳሳተ መንገድ መተቸቱና መኮነኑ መሰረተ ቢስና ተቀባይነት የሌለው ነው” ሲሉ የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ ተናግረዋል፡፡

ዋና አስተዳዳሪው አቶ ደሳለኝ ጣሰው፣… ከፍተኛ ጀብድ ለሠራ የአማራ ልዩ ኃይል ምሥጋናና እውቅና ሊሰጠው ሲገባ በአንዳንድ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለምንግዜም የአማራ እና የኢትዮጵያ ጠላት ለሆኑት ለተደመሰሰው የጁንታው ኃይልና ለኦነግ ሸኔ ማይክ ለመሆን የአማራ ልዩ ኃይልን በተሳሳተ መንገድ መተቸቱና መኮነኑ መሰረተ ቢስና ተቀባይነት የሌለው መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳህሉ በበኩላቸው፣ “የአማራ ልዩ ኃይል ለአማራ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያም ደጀን መሆኑን በተግባር ያረጋገጠ ኃይል ነው” በማለት ገልፀው፣ “አንዳንድ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በፓርላማ ውስጥ የሚያራግቡት ሀሳብ የተላላኪነት ሚናቸውን ለመጫወት ካላቸው ፍላጎት የመነጨ ነው። ስለ ልዩ ኃይሉ ግብረ-ገብነትና ሕዝባዊነት በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በተወሰደው ሕግ ማስከበር ዘመቻ ወቅት የሀገር መከላከያ ሠራዊትና የጁንታው ምርኮኞች በተግባር ያረጋገጡት እውነታ ነው” ብለዋል።

በተመሳሳይ፣ የሀገር ባለውለታ የሆነውን የአማራ ልዩ ኃይል ስም በማጠልሸት ጁንታዉ ከመቃብር የሚነሳ የሚመስላቸው ተላላኪዎች ከድርጊታቸው ሊታቀቡ እንደሚገባ የምሥራቅ ጎጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪ አሳስበዋል፡፡

ዋና አስተዳዳሪው አቶ አብርሃም አያሌዉ እንደገለጹት የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች እርስ በእርስ እንዲጠራጠሩ የጥላቻ መርዝ እንዲረጭ ያደረጉ የፓርላማ አባላት በአሠራርና ሥነ ምግባር መመሪያው መሰረት በሕግ ሊጠየቁ እንደሚገባም አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ክብር ዝቅ እንዲል የሚፈልጉ የውጭና የውስጥ ተላላኪዎች በአማራ ልዩ ኃይል ላይ የሚያካሄዱት የስም ማጥፋት ዘመቻ እንደ ብረት የሚያጠነክረውና አንድ የሚያደርገው እንደሆነና ለጁንታዉ ተላላኪዎች ጆሮ የማይሰጥ፣ ኢትዮጵያንም ለድርድር የማያቀርብ የሀገር አለኝታ መሆኑንም ነው ዋና አስተዳዳሪው ያስታወቁት።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በፓርላማው ከስነምግባር ደንቡ ውጪ የሆነ ሃሳብና ጥያቄ አንስተዋል ከተባሉት የምክር ቤቱ አባላት አንዱ፣ ቀደም ብለው ለፓርላማው ኮሚቴ ካስገቡትና ከተፈቀደላቸው ጥያቄ ውጪ በራሳቸው ተነሳሽነት ለአሁኑ ውዝግብ መነሻ የሆኑትን ጥያቄዎች ማቅረባቸው እየተነገረ ሲሆን፣ “ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የማቀርበው ነው” በሚል የካቲት 22 ቀን 2013 ዓ.ም ባስገቡት የፅሁፍ ንግግራቸው ውስጥም በስብሰባው ያቀረቡት ሃሳብና ጥያቄ አለመካተቱ ተመልክቷል። የፖርላማው አፈ ጉባዔ የምክር ቤቱ አባል ከአጀንዳ መውጣታቸውን ተረድተው በፍጥነት አለማስቆማቸውም ለትችት ዳርጓቸዋል።

ከዚሁ ጋር ተያያዥ በሆኑ ገዳዮች ዙሪያ የኦሮሞ ብልጽግና እና  የአማራ ብልፅግና የተካረሩ መገለጫዎችን መወጣታቸው ይታወቃል።

LEAVE A REPLY