“ማስክ ያላደረገ ሰው ምንም አገልግሎት እንዳያገኝ” ተባለ

“ማስክ ያላደረገ ሰው ምንም አገልግሎት እንዳያገኝ” ተባለ

ኢትዮጵያ ነገ ዜናበኢትዮጵያ ከቀን ወደቀን እየተባባሰና ከሀገሪቱ አቅም በላይ ሆኖ የሚገኘውን የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ለመግታት፣ የጤና ሚኒስቴር እና የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ” በወንጀል እስከመጠየቅ የሚያደርስ በሰዎች እንቅስቃሴና ማህበራዊ ተግባራት ላይ ክልከላ የሚጥል አዲስ መመሪያ” ይፋ አድርገዋል::

የጤና ሚኒስቴር እና የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ዛሬ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደገለፁት፣ ማንኛውም የኮሮና ቫይረስ ያለበት ግለሰብ ወደ ሃገር ውስጥ እንዳይገባ፣ ቫይረሱ የተገኘበት ሰውም ወደ ማህበረሰቡ እንዳይቀላቀል፣ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘም ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ፤ ቫይረሱ ሊተላለፍ በሚያስችል ሁኔታም ንክኪ ማድረግ በህግ የሚያስቀጣ መሆኑ በአዲሱ መመሪያ ተከልክሏል::

“በየትኛውም ቦታ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ሳያደርግ መንቀሳቀስ የተከለከለ ነው፣ የንግድና ሌሎች የአገልግሎት ሰጪ ተቋማትም ማስክ ያላደረገ ሰውን እንዳያስተናግዱ” የሚያስገድደው መመሪያው፣

“የትራንስፖርትና የስፖርት እንዲሁም ሌሎች ማህበራዊ መሰባሰቦችን በሚመለከት ተቋማቱ በሚያወጧቸው ዝርዝር ደንቦች የሚፈፀሙ ይሆናል” ሲል ደንግጓል።
“መመሪያውን ተግባራዊ የማያደርጉ አካላት እስከ 3 ዓመት በሚደርስ እስራት እንዲሁም ሌሎች ቅጣቶች እንደሚጣልባቸው” ተመልክቷል።

ስብሰባን በሚመለከትም ማንኛውም ሰብሳቢ አካል ተገቢውን የቅድመ መከላከል ተግባራትን እንዲከውንና የተሰብሳቢዎች ቁጥርም 50 ብቻ እንዲሆን መወሰኑን አስታውቋል።

አዲሱ አስገዳጅ የክልከላ መመሪያ ከመጪው ሰኞ ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ በጋራ መግለጫው ተገልጿል።

LEAVE A REPLY