የወርቅ ኒሻን፣ የመኪናና የገንዘብ ሽልማት ተበረከተላት!
ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ትናንት መጋቢት 19/2013 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስካይ ላይት ሆቴል ለኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ በተዘጋጀ የክብር ፕሮግራም 350 ግራም የሚመዝን ሀገር አቀፍ የክብር የወርቅ ኒሻን ሽልማት ለአትሌቷ ተበርክቶላታል።
ከኒሻኑ በተጨማሪም 2021 ሞዴል ሌክሰስ ቪ8 መኪና በአገር አቀፍ ደረጃ የተበረከተላት ሲሆን፣ በስነ-ስርአቱ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አያት አደባባይን በስሟ ሰይሞ ለማልማት መወሰኑን ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል። የከተማ አስተዳደሩ አደባባዩን ለማልማትም 2 ሚሊዮን ብር መድቧል ብለዋል።
በሌላ በኩል፣ በአዳማ ከተማ የሚገኘው ትልቁ አደባባይ በኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ መሰየሙን ያስታወሱት የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣ በአንድ ቢሊዮን ብር የተገነባው የሱሉልታ አካዳሚም በስሟ መሰየሙን አብስረዋል።
በዚሁ ፕሮግራም ላይ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት 5 ሚሊዮን ብር ለባርሴሎናዋ ጀግና የሸለመ ሲሆን አትሌት ደራርቱም ለተደረገላት ክብር ሁሉ ምስጋናዋን አቅርባለች።