ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ወደከፍተኛ ትምህርት መግቢያ የሚሆነው የ12ኛ ክፍል ፈተና ውጤት ከነገ ጀምሮ ይፋ እንደሚደረግ ሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡
ኤጀንሲው የ2012 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና የውጤት ትንተና መግለጫ ዛሬ የሰጠ ሲሆን፣ በፈተናው ከ600 በላይ ያመጡ ተማሪዎች ቁጥር 702 መሆኑን፣ 521 ወንድ እና 181 ሴት ተማሪዎች ከ600 በላይ ውጤት ማምጣታቸውን እንዲሁም የዓመቱ ከፍተኛ ውጤት 669 ሆኖ መመዝገቡን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ዲላሞ ኦተሪ አስታውቀዋል።
በዛሬው መግለጫ እንደተመለከተው፣ ተፈታኝ ተማሪዎች ውጤታቸውን በፈተናዎች ኤጀንሲ ድረ ገጽ እንዲሁም በአጭር የጽሑፍ መልዕክት 8181 የፈተና መለያ ቁጥራቸውን በማስገባት ከነገ ጀምሮ መመልከት ይችላሉ።