የሱማሌ ክልልና የምርጫ ቦርድ አለመግባባት እየተካረረ ነው!

የሱማሌ ክልልና የምርጫ ቦርድ አለመግባባት እየተካረረ ነው!

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– የሱማሌ ክልላዊ መንግስት ከአጎራባቹ የአፋር ክልል ጋር ለአመታት ሲወዛገብባቸውና አልፎ አልፎም የግጭት መነሻ ሆየው የቆዩ 8 አዋሳኝ ቀበሌዎችን ላይ ምርጫ እንዳይካሄድ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ውሳኔ መተላለፉን ተቃውሟል።

“ውሳኔው ካልተሻረ በምርጫው ለመሳተፍ እቸገራለሁ” የሚል መግለጫ ማውጣቱን ከቀናት መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን፣ ጉዳይ አሁንም ያልተፈታና ይልቁንም በቦርዱና በክልሉ አስተዳደር መካከል የተፈጠረው አለመግባባት እየተባባሰ መምጣቱን በሁለቱም በኩል ከሚወጡ መረጃዎች መታዘብ ይቻላል።

እንደ መረጃዎቹ ከሆነ፣ በምርጫ ቦርድና በሱማሌ ክልል መካከል አለመግባባቱ እንዲከሰት ምክንያት የሆነው፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ ጣቢያዎችን ዝርዝር ይፋ ባደረገበት የየካቲት 18 ቀን 2013 ዓ.ም መግለጫው የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትን ለቅሬታ መጋበዙና ክልሉ “የምርጫ ጣቢያዎች ያለአግባብ በሶማሌ ብሔራዊ ክልል መንግስት ስር በሚገኙ ቀበሌዎች ስም ይፋ ተደርገዋል” የሚል አቤቱታ ለቦርዱ ማቅረቡ ሲሆን፣ አቤቱታ የቀረበለት ምርጫ ቦርድ የመራጮች ምዝገባ ከመጀመሩ በፊት አቤቱታውን ተመልክቶ በስምንቱ ቀበሌዎች ስር በተቋቋሙ 30 የምርጫ ጣቢያዎች ምርጫ ላለማድረግ ከውሳኔ ላይ መድረሱን ማሳወቁ የአለመግባባቱ ዋነኛ መነሻ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

የሱማሌ ክልል የምርጫ ቦርድን ውሳኔ በመቃወም “በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተወሰነው ውሳኔ በሱማሌ ከልላዊ መንግስት በኩል ተቀባይነት የሌለው መሆኑን እየገለፅን ቦርዱ የአካባቢውን ነባራዊ ሁኔታና በተጨባጭ ያለውን እውነት በጥልቀት በመርመር የወሰነውን ለአንድ ወገን ያደላ ኢ-ፍትሐዊ ውሳኔ በመሻር ከዚህ በፊት በነበሩት 5 አገራዊ ምርጫዎች ሲደረግ በነበረው አግባብ የምርጫ ጣቢያዎቹን እንዲቋቋሙ እያሳሰብን ይህ የማይሆን ከሆነ በአገራዊ ምርጫው ለመሳተፍ የምንቸገር መሆኑን እናሳውቃለን” ሲል መግለጫ ካወጣ በኋላ ቦርዱ በበኩሉ በሰጠው ምላሽ “…እንደሚታወቀው ምርጫ ጣቢያዎች ዜጎች ድምጻቸውን ለመስጠት የሚመቻቹ የመመዝገቢያ እና ድምጽ መስጫ ቦታዎች ሲሆኑ፣ የየትኛውም የመንግስት አስተዳድር መዋቅር አካላት አይደሉም።

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም በሚያከናውናቸው የምርጫ ኦፕሬሽን ተግባራት በተለያዩ ደረጃዎች የራሱን መዋቅር የሚያዘጋጅ ሲሆን እነዚህ መዋቅሮች ከመንግሰት ቋሚ መዋቅር ጋር ተመሳሳይነት የላቸውም። ቦርዱ ከላይ የተጠቀሱትን ጥሬ ሃቆች እና አሰራሮች ከግምት ውስጥ በማስገባት የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የቀረበውን የምርጫ ክልሎች አላግባብ በሶማሌ ክልል ውስጥ በሚገኙ ቀበሌዎች ተጠርተዋል የሚለውን የካቲት 05 ቀን 2013 በተጻፈ ደብዳቤ የቀረበውን አቤቱታ መርምሯል” በማለት ገልፆ “…ምንም አንኳን ከላይ እንደተጠቀሰው ቦርዱ በ2007 ዓ.ም የተጠቀመበትን የመረጃ ዝርዝር ለ6ተኛው አገራዊ ምርጫ ቢጠቀምም፣ የምርጫ ጣቢያዎች የአስተዳደር ወሰኖችን የሚወስኑ መገለጫዎች ባይሆኑም ቦርዱ ምርጫ በምንም መልኩ የሰላም መደፍረስ ምክንያት እንዳይሆን በማሰብ
• በጋላእቶ/አዳይሌ
• በአዳይቱ/አዳይቱ
• በቴውኦ/አላሌ
• በጉርሙዳሊ/ዳንሌሄላይ
• በኡንዳፎኦ/ኡንዱፎ
• በጋዳማይቱ/ጋርባኢሴ
• በአፍዓሶ/አፉአሴ
• በባላእቲ ጎና/መደኒ
ቀበሌዎች ሊከፈቱ የነበሩትን 30 የምርጫ ጣቢያዎች በአካባቢው እንዳይቋቋሙ ወስኗል።


በዚህም መሰረት በአካባቢው የሚኖሩ እና የመራጮች ምዝገባ እና የድምጽ መስጠት ሂደት ውስጥ የሚሳተፉ ዜጎች በአቅራቢያቸው ባለ ሌላ ቀበሌ መመዝገብ እና ድምጻቸውን መስጠት የሚችሉ ሲሆን ይህንን ተግባራዊ እንዲያደርጉ ቦርዱ ለምርጫ አስፈጻሚዎቹ ተገቢውን መመሪያ የሚያስተላልፍ ይሆናል” ሲል አስታውቋል።

በተያያዘ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለሁለተኛ ጊዜ ምላሽ መስጠቱን ተከትሎ የሱማሌ ክልል ተወላጆች አደባባይ ወጥተው የቦርዱን ውሳኔ መቃወም ጀምረዋል። ትናንት ለሶስተኛ ቀን ባደረጉት የተቃውሞ ሰልፍም “የምርጫ ቦርድ ውሳኔ ኢ ፍትሐዊ ነው፤ ሙስጠፌ መሐመድ እናመሰግናለን” የሚሉና ሌሎች በርካታ መፈክሮችን ሲያሰሙ መዋላቸው ታውቋል።
በክልሉ መንግስት የሚመሩ ሚዲያዎችም የተቃውሞ ሰልፉን በሚመለከት “የመምረጥ ህገ መንግስታዊ መብታቸው ያለ አግባብ በኢ-ፍትሃዊ ውሳኔ በምርጫ ቦርድ በማንነታችው፤ ሶማሌ በመሆናቸው ብቻ የተነጠቁት ዜጎቻችን ዛሬም ለ3ተኛ ቀን በሰላማዊ ሰልፍ ድምፃችን ይሰማ!!! የምርጫ ቦርድን ውሳኔ አንቀበልም እያሉ ነው” የሚል ዘገባ አሰራጭተዋል።
ይሁንና የክልሉ ምክትል ፕ/ት አቶ ሙስጠፌ መሐመድ ጉዳዩን በሚመለከት ባስተላለፉት መልዕክት “ኢትዮጵያ የሚለው ስም!…የክልሉ መንግስት በሶማሌ እና በአፋር መካከል የተፈጠሩ የድንበር ውዝግቦችን ለመፍታት እንደ ሁልጊዜው ዛሬም ቁርጠኛ ነው!…በሀገር ጉዳይ በጭራሽ አንደራደርም።…ከሁሉም በላይ አንድ የሚያደርገን ኢትዮጵያ የሚለው ታላቅ ስም ነው! ይኄው ነው‼” የሚል መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን፣ መልዕክቱ ዝርዝር ጉዳዮች ከመነካካት የተቆጠበ መሆኑ በአንዳንድ የፖለቲካ ታዛቢዎች ዘንድ ስጋት የሚጭር ሆኗል።


ከቀናት በፊት የክልሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት የክልሉ ልዩ ኃይል አዲስ ሰልጣኞችን ባልተለመደ መልኩ መጎብኘታቸው በራሱ በቀጣይ ምን ሊፈጠር ይችላል የሚል ስጋት እንደሚጭር የጠቀሱት እነዚሁ ታዛቢዎች የፌደራሉ መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት የሱማሌ ክልል፣ የአፋር ክልልና ምርጫ ቦርድ ተቀራርበው በልዩነቶቻቸው ላይ ግልፅ ውይይት ማድረግ የሚችሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንዳለበት አሳስበዋል።

LEAVE A REPLY