ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ተጠርጥረው ከተከሰሱት መካከል ሶስተኛው ተከሳሽ በዋስት እንዲለቀቅ መወሰኑ ታወቀ።
የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የፀረ-ሽብርና ህገመንግስት ጉዳዮች ወንጀል ምርመራ ችሎት ዛሬ በሰጠው ትዕዛዝ፣ አብዲ ዓለማየሁ የተባለው ሶስተኛው ተከሳሽ የቀረበበት ክስ የዋስትና መብቱን የሚያስከለክል ባለመሆኑ 10 ሺህ ብር ዋስትና አስይዞ ከእስር እንዲለቀቅ ወስኗል፡፡
ከሌሎች ተከሳሾች ጋር በአቃቤ ህግ የሽብር ወንጀል ተመስርቶበት የቆየዉ አብዲ ዓለማየሁ በዚሁ ፍርድ ቤት የካቲት 18 ፣ 2013 ዓ.ም በዋለው ችሎት የተከሰሰበት የሽብር ወንጀል ተሻሽሎ ግድያውን ለፍትህ አካላት ባለማሳወቁ 1996 በወጣው የወንጀል ህግ አንቀጽ 443/1 መሰረት እንዲጠየቅ ተወስኖ እንደነበር ይታወሳል። ከሳሽ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ባልታደመበት ዛሬ በዋለው ችሎት ተከሳሹ የተመሰረተበት ክስ ከተረጋገጠ ከስድስት ወራት ባልበለጠ ቀላል እስራት ብቻ የሚያስቀጣ በመሆኑ፤ ተከሳሽ እስካሁን ለዘጠኝ ወራት በእስራት በመቆየቱ የዋስትና መብት የሚያስከለክል ሆኖ አለማግኘቱን ፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡
በተያያዘ፣ አንደኛ ተከሳሽ ጥላዬ ያሚ እና ሁለተኛ ተከሳሽ ከበደ ገመቹን ጨምሮ ከአንደኛ አስከ ሶስተኛ ያሉ ተከሳሾች፤ ዛሬም ተከላካይ ምስክሮቻቸውን ያላቀረቡ ሲሆን፣ ተከሳሾቹ ትናንት በዋለው ችሎት ከምስክሮቻቸው ጋር መገናኘት አለመቻላቸውን ገልጸው ተለዋጭ ቀጠሮ ለዛሬ ተሰጥቷቸው ነበር፡፡ ይሁንና ዛሬም ተከሳሾቹ ከተከላካይ ምስክሮቻቸው ጋር ተገናኝተው ለመነጋገር በቂ ጊዜ አለማግኘታቸውን በጠበቃቸው በኩል በመግለፃቸው ፍርድ ቤቱ ለሚያዚያ 6 ቀን 2013ዓ.ም የመጨረሻ ቀጠሮ ሰጥቷል።