ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ከቻይና መንግስት ለኢትዮጵያ የተለገሰውን 300 ሺህ ዶዝ “ሲኖፋም” የተባለ የኮቪድ-19 ክትባት፣ የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰና ሌሎች ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ከሆኑት ዣዎ ዢውሃን ዛሬ አስረክበዋል።
በርክክብ ስነ ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ፣ አሁን ከቻይና መንግስት የተገኘው የክትባት ድጋፍ ወረርሽኙን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረትና እንደ ሀገር 20 ሚሊዮን ሰዎችን በክትባት ለመድረስ የተያዘውን እቅድ ለማሳካት የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።
የቻይና አምባሳደር ዣዎ ዢውሃን በበኩላቸው፣ ሁለቱ ሀገራት ከመጀመሪያው ጀምሮ ወረርሽኙን የመከላከል ስራውን በጋራ ሲሰሩ መቆየታቸውን ጠቁመው በኢትዮጵያ አሁንም ወረርሽኙ እያደረሰ ያለውን ጫና ለመቋቋም በትብብር መስራታቸውን እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።