ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ኬሮ ኦድ የስፖርትና ልማት ማህበር ከጉራጌ ልማት ማህበር ጋር በመተባበር የ15 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር ለማካሄድ መሰናዶው እንደተገባደደ ተገለፀ።
ዛሬ ከሰዓት በኋላ በአዲስ አበባ ኤሊያና ሆቴል በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ እንደተገለፀው፣ ግንቦት 8/2013 የሚካሄደው የሩጫ ውድድር “ሰላምና አንድነት ለኢትዮጵያ ህዝብ” የሚል መሪ ቃል የተሰጠው ሲሆን፣ 300 አትሌቶችና 10 ሺህ ዜጎች ተሳታፊ ይሆናሉ ተብሏል።
የአዘጋጁ ኬሮ ኦድ የስፖርትና ልማት ማህበር የስራ ኃላፊዎችና የጉራጌ ክልል ተወላጅ የሆኑ ፕሮፌሽናል ወጣት አትሌቶች በጋራ በሰጡት መግለጫ እንደተመለከተው፣ ወድድሩ ወልቂጤ ዩንቨርስቲን መነሻ አድርጎ ወልቂጤ ከተማ ላይ የሚጠናቀቅ ሲሆን፤ የወልቂጤ ዩንቨርስቲ ፣ ቢጂአይ ኢትዮጵያና ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ለውድድሩ ስኬት የገንዘብ እገዛ ማድረጋቸው ተመልክቷል።
በዛሬው መግለጫ ላይ በክብር እንግድነት የተጋበዙት አትሌት ስለሺ ስህን፣ አትሌት አሰፋ መዝገቡና አሰልጣኝ ኮማንደር ሁሴን ሽቦ በውድድሩ መዘጋጀት የተሰማቸውን ደስታ ገልፀው፣ እንዲህ ያሉ ውድድሮች ከስፖርታዊ የጤና ጠቀሜታቸው በላይ ማህበራዊ ግንኙነትንና አገራዊ አንድነትን በማጠናከር በኩል ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው ገልፀዋል።