ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ልዩ ቦታው ትንሹ መናኸያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ መጋቢት 20 ቀን 2013 ዓ.ም 1,400 የክላሽ ጥይት መያዙ ተነግሯል።
ጥይቱ የተያዘው አንድ ግለሰብ ጥይቶቹን በባለ10 ሊትር ጀሪካን ውስጥ በማድረግ ከፒያሳ ወደ አውቶቡስ ተራ በሚጓዝ ታክሲ ተሳፍሮ መርካቶ አካባቢ እንደደረሰ ጥይቱን በተለምዶ “ትንሹ መናኸሪያ” እንዲያደርስለት ለአንድ የቀን ሰራተኛ በማሸከሙ ሲሆን፣ የተሸከመው ዕቃ ከዘይት ያለፈ ክብደት እንዳለው የተጠራጠረው የቀን ሰራተኛ ጉዳዩን በአካባቢው ላገኛቸው የፀጥታ አካላት በማሳወቁ ጀሪካኑ ተከፍቶ ሲታይ አንድ ሺ አራት መቶ ስድስት የክላሽንኮቭ ጠመንጃ ጥይት እንደሆነ ተረጋግጧል።
በጉዳዩ ዙሪያ ምርመራ እያደረገ እንደሚገኝ ያሳወቀው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፣ ለቀን ሰራተኛውና ለየአካባቢው ታክሲ ተራ አስከባሪዎች ይህ የወንጀል ድርጊት እንዲጋለጥ በማድረጋቸው ምስጋና አቅርቧል።