ትናንት ምሽት በወለጋ በተፈፀመ “ዘር ተኮር ጥቃት” በርካታ ንፁሃን መገደላቸው ተነገረ!

ትናንት ምሽት በወለጋ በተፈፀመ “ዘር ተኮር ጥቃት” በርካታ ንፁሃን መገደላቸው ተነገረ!

ኢትዮጵያ ነገ ዜናበኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ባቦ ጋምቤል ወረዳ፣ ቦኔ ቀበሌ፣ ትናንት ምሽት 3 ሰዓት ላይ በተከፈተ ዘርን መሠረት ያደረገ ጅምላ ጭፍጨፋ በርካታ ንጹሃን ዜጎች መገደላቸውን ከአካባቢው የተገኙ መረጃዎች አመላክተዋል።

ከጭፍጨፋው ከተረፉ የዓይን እማኞች ያገኙትን መረጃ እያጋሩ ያሉ መገናኛ ብዙሃን እንደሚገልፁት፣ አሁን ላይ አስክሬኖች በየቦታው ተጥለው የሚታዩ ሲሆን የሟቾች ቁጥር ምን ያህል ነው የሚለውን ለመግለጽ አስቸጋሪ ነው ተብሏል፡፡
ሕጻናትና ሴቶች ህይወታቸውን ለማትረፍ ወደ ጫካዎች መግባታቸውን የገለጹት ምንጮች፣ መንግስት የማይደርስላቸው ከሆነ አሁንም ሌላ ግድያ ሊኖር እንደሚችል ስጋታቸውን እየገለፁ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

የአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት በበኩሉ፣ ትናንት ምሽት በምዕራብ ወለጋ ዞን ባቦ ገንቤል ወረዳ ቦኔ ቀበሌ በንጹሐን አማራዎች ላይ የጀምላ ጭፍጨፋ መፈፀሙን ከጥቃት የተረፉ ነዋሪዎች እንደነገሩት ገልፃ፤ “ትናንት ምሽት 1 ስዓት አካባቢ የታጠቁ የኦነግ ሸኔ አባላት ወደ ነዋሪዎቹ ቀየ ዘልቀው በመግባት ንጹሐን አማራዎች ላይ ጭፍጨፋ ፈጽመዋል” ብሏል፡፡

“ነዋሪዎቹ ከዚህ ቀድሞ አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ሲዛትባቸው እንደነበር ገልፀው ትናንት ምሽት ዘር ተኮር የሆነ የጅምላ ጭፍጨፋ ተፈፅሞብናል ብለዋል” ሲል አያይዞ የዘገበው አብመድ፣ የአይን እማኞቹ “ከምሽቱ 4 ስዓት ጀምሮ የጸጥታ ኃይል በአካባቢው ቢደርስም እርምጃ እንድንወስድ ስላልታዘዝን ራሳችሁን ጠብቁ በሚል ብቻ መመለሳቸውንና መንግሥት በአፋጣኝ ደርሶ እንዲታደጋቸው መጠየቃቸውንም” አስታውቋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የኦሮምያ ክልል መንግሥት በአካባቢው በኦነግ ሽኔ ግድያ መፈጸሙን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

“…የጁንታው ተላላኪው ኦነግ ሸኔ የጥፋት ሰንሰለቱን በገጠርና በከተማ በማስፋት በመንግስት አመራሮችና በሰላማዊ ዜጎች ላይ ዘግናኝ የሽብር ጥቃቶችን ሲፈፅም ቆይቷል፡፡ በዚህም ሳቢያ የብዙ ንፁሃን ዜጎች ህይወት አልፏል፡፡ ከቀበሌ እስከ ክልል አመራር ድረስ የጥቃቱ ሰለባ ሆነዋል፡፡አያሌ የግልና የመንግስት ንብረቶች ወድመዋል፡፡ የዚህን የኦነግ ሸኔ እኩይ ተግባር ለማስወገድ መንግስት በወሰደው የህግ የበላይነትን የማስከበር እርምጃ ሀይሉ እየተዳከመ የሄደ ቢሆንም በሞትና በህይወት መካከል ሆኖ የጥፋት ሴራውንና እርምጃውን ቀጥሏል” የኦሮምያ ክልላዊ መንግሥት መግለጫ “በትናንትናው ዕለት በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ባቦ ገንቤል ወረዳ በቦኔ ቀበሌ በወሰደው የሽብር ጥቃት ለግዜው ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ዜጎች በጥቃቱ ህይወታቸው አልፏል፡፡

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሰት በዚህ አሰቃቂና ዘግናኝ ጥቃት የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን እየገለጸ ለተጎጂ ቤተሰቦችና ዘመዶቻቸው መጽናናትን ይመኛል፡፡ የክልል መንግሰት ድርጊቱ በተፈጸመበት አካባቢ በፍጥነት በመድረስ በወሰደው እርምጃ በጥቃቱ አድራሾች ላይ የአጸፋ እርምጃ የወሰደ ሲሆን በቀጣይነትም የሚወሰዱ እርምጃዎችን ለሕዝብ ይፋ እንደምናደርግ ከወዲሁ እንገልጻለን” በማለት አስታውቋል።

ተስፋ የቆረጠው ኦነግ ሸኔ ህዝብ ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ፈፅሟል-የኦሮሚያ ክልል ፓሊስ በተያያዘ፣ የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ከሰዓታት በፊት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ “ተስፋ የቆረጠው ኦነግ ሸኔ ህዝብ ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ፈፅሟል” ብሏል።

መግለጫውን የሰጡት ኮሚሽነር አራርሳ መርዳሳ፤ ኦነግ ሸኔ በምዕራብ ወለጋ ገንቤል ትናንት ምሽት 3 ሰአት አካባቢ “ነዋሪዎችን ከቤታቸው በግድ በማስወጣት በአንድ ቦታ ላይ አግቶ የተኩስ እሩምታ በመክፈት ጥቃት ፈፅሞባቸዋል” ብለዋል።

“ቡድኑ በዚህ ድርጊቱ የለየለት ሽብርተኛ መሆኑን አሳይቷል” ያሉት ኮሚሽነር አራርሳ፣ በጥቃቱም 28 ሲሞቱ 12ቱ መቁሰላቸውን አመልክተው፤ ጥቃቱ የኦሮሞም የአማራም ተወላጆች ላይ መፈጸሙን ተናግረዋል። ሁኔታው ከተከሰተ በኋላ ለማረጋጋት በስፍራው የደረሰው ሃይል በወሰደው እርምጃ 3 የኦነግ ሸኔ ከነትጥቃቸው መደምሰሳቸውን እና ቀሪ ጥቃት ፈፃሚዎቹን እና ርዝራዡን ለመያዝ እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

 

LEAVE A REPLY