ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ዛሬ ጠዋት በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ሀይሌ ጋርመንት አካባቢ በሚገኘው አትክልት ተራ፣ በሁለት ግለሰቦች መካካል በተፈጠረ ፀብ የአንድ ሰው ህይወት ማለፉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ገልጿል።
ከጠዋቱ በግምት 2፡00 ሰዓት አካባቢ በሁለት የጉልበት ሰራተኞች መካከል በስራ አለመግባባት ምክንያት በተፈጠረ ፀብ የአንደኛው ሕይወት ማለፉን እና ገዳዩ በቁጥጥር መዋሉን ያመለከተው ፖሊስ፣ የተወሰኑ ግለሰቦች የግድያ ወንጀል በፈፀመው ተጠርጣሪ ላይ ጉዳት ለማድረስ በፈጠሩት ፀብ ምክንያት በፖሊስ አባላትና በአካባቢ ጥበቃ ስራ በተሰማሩ አጋዥ ሀይሎች ላይ ጉዳት መድረሱም ተገልጿል፡፡
ግርግሩን ለማብረድ ፖሊስ ባደረገው ጥረት አካባቢው ተረጋግቶ መደበኛ ሰራ መጀመሩን እና ግርግር በማስነሳት ጉዳት እንዲደርስ ያደረጉ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ኮሚሽኑ አመልክቶ፣ “ይሁንና በአንዳንድ ማህበራዊ ሚዲያዎች በሁለት ብሔሮች መካከል ፀብ እንደተነሳ ተደርጎ እየተናፈሰ ያለው መረጃ ሀሰተኛ ነው” ሲል አስታውቋል።