በተለያዩ ጊዜያት ዘርን መሰረት አድርገው ለሚፈፀሙ ጥቃቶች መንግስትና አንዳንድ አካላት ኦነግ ሸኔን በስም ጠቅሰው በተጠያቂነት መወንጀላቸው የሚታወቅ ሲሆን፣ ከቀናት በፊት በምዕራብ ወለጋ የተፈፀመውን የዘር ጭፍጨፋ የፈፀመውም በኦነግ ሸኔ እንደሆነ በርካታ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ ባለስልጣናት መግለፃቸውና ጥቃቱን በሚመለከት የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን በሰጠው መግለጫ “ተስፋ የቆረጠው ኦነግ ሸኔ ህዝብ ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ፈፅሟል” ማለቱ ይታወቃል።
የምዕራብ ወለጋ ዞን ፀጥታ እና አስተዳደር ፅ/ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ አብዩ ምህረቱ በበኩላቸው የሰሞኑ ግድያ የተፈፀመው በኦነግ ሸኔ እንደሆነ ገልፀው “ጥቃት ከፈፀሙት ውስጥ 3ቱ በፀጥታ ኃይሎች ተገድለው የኦነግ ሸኔ ታጣሪዎች ናቸው፤ ህብረተሰቡ እንዲያቸው ተደርጓል…ንፁሃንን እየገደለ ያለው ኦነግ ሸኔ ስለመሆኑ ምንም የሚያጠራጥር ነገር የለም፤ ተጨባጭና ህብረተሰቡ የሚናገረው መሬት ላይ ያለ እውነታ ነው” ሲሉ አስረግጠው ተናግረዋል።
ይሁንና “የኦነግ ሸኔ መስራችና መሪ ናቸው” የሚባሉት አቶ ኩምሳ ድሪባ (ጃል መሮ) ትላንት ምሽት ለአሜሪካ ድምፅ ሬድዮ በሰጡት ቃል”ኦነግ ሸኔ ስለሚባል ነገር አይመለከተኝም፤ በማያገባን ጉዳይ ሳንጠራ አቤት ምንልበት ምክንያት የለም፤ እኛ የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ነን፤ በዚህ ስም የቀረበብን ክስ የለም” ሲሉ ገልፀው “ኦነግ በንፁሃን ግድያ እጁን አያስገባም። በሰራዊቱ የተከሰተ ግድያ የለም። አንድን ብሄር መሰረት ያደረገ ቀርቶ አንዲት ነብስ በኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት እጅ ቢጠፋ ከባድ ተጠያቂነት ነው ያለው” ብለዋል።
“መወቃቀሱ መወነጃጀሉ ለነኚህ ለሚያልቁት አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ አንበል ኢትዮጵያዊም አንበል፤ ለሚያልቁት ንፁሃን የእግዜር ፍጡራን መጫወቻ ቁማር መሆን የለበትምና እንዲህ ያለው ግድያ ኢትዮጵያ ውስጥ በዝቷል ገለልተኛ አካል ያጣራ” ሲሉ ከገለፁ በኋላ አያይዘውም “ጃል መሮ ተደገለ ተብሎ የሚወራው ሀሰት ነው”ብለዋል።