የጋዜጠኛ ከተማ ኃይለማርያም ስንብት!

የጋዜጠኛ ከተማ ኃይለማርያም ስንብት!

ኢትዮጵያ ነገ ዜናበኢትዮጵያ ነፃ ፕሬስ ውስጥ በጋዜጣ አዘጋጅነት የቀደመ ሚና የነበረውና በኋላም የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ባልደረባ ሆኖ ረጅም ለዓመታት ያገለገለው ጋዜጠኛ ከተማ ኃይለማርያም መጋቢት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።

ጋዜጠኛ ከተማ ለኪነ-ጥበብ እና ጋዜጠኝነት በነበረው ልዩ ፍቅር እና ተሰጥኦ መነሻነት ከለጋ እድሜው ጀምሮ በተማረባቸው ትምህርት ቤቶች ውስጥ በሚኒ-ሚዲያ እና ሌሎች ክበባት ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ያደርግ የነበረ ሲሆን፣ በጳውሎስ አማተር ጋዜጠኞች ማህበር በኩል ወደ ፕሮፌሽናልነት በተሻገረው ረጅም የሙያ ህይወቱ በነፃ ፕሬስ ጋዜጦች፣ በቀድሞው የኢትዮጵያ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ድርጅትና በአሁኑ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ያልሰራባቸው የፕሮግራም ክፍሎች የሉም ማለት ይቻላል።

ጋዜጠኛ ከተማ ኃይለማሪያም እንደብዙዎቹ ጋዜጠኞች የተለመዱ የፕሮግራም እና ዜና ዘገባዎችን ከመስራት በዘለለ፣ የህብረተሰቡን የእለት ተዕለት ችግሮች በማድመጥ ኮርኳሪ ውይይቶችን የሚያዘጋጅ፣ ለሚመለከታቸው የስራ ኃላፊዎች ሞጋች ጥያቄዎችን የሚወረውር፣ ችግሮች መፍትሄ እስኪያገኙ ብዙ ርቀት የሚሄድ፣ ለህዝብ የወገነ ጋዜጠኛ ነበር።

ልክ የዛሬ ስድስት ወር በዚች እለት የሁለት ልጆቹን እናት፣ ባለቤቱን ወይዘሮ እቴነሽ መኮንንን በሞት ያጣው ጋዜጠኛ ከተማ፣ ባደረበት ህመም ምክንያት ለቀናት በህክምና ሲረዳ ቆይቶ፣ መጋቢት 24 ቀን 2013 ዓመተ ምህረት፣ በተወለደ በ45 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቶናል። ስርዓተ ቀብሩም በቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን ዛሬ 9:00 ሰዓት ላይ ተፈጽሟል።

የኢትዮጵያ ነገ ዝግጅት ክፍል፣ በታታሪው ጋዜጠኛ ከተማ ኃይለማሪያም ህልፈት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን እየገለፀ፤ ለቤተሰቡ ለሙያ ጓደኞቹና ወዳጆቹ መጽናናትን ይመኛል።

LEAVE A REPLY