የአማራና የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ አመራሮች በሰላምና ፀጥታ ጉዳይ የጋራ ስብሰባ ተቀመጡ!

የአማራና የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ አመራሮች በሰላምና ፀጥታ ጉዳይ የጋራ ስብሰባ ተቀመጡ!

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– የአማራ እና የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ከፍተኛ አመራሮች በሁለቱ ክልሎች የጋራ ሠላም እና የልማት አጀንዳዎች ላይ ሲመክሩ መዋላቸው ተገለፀ።

በምክክር መድረኩ በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች በተደጋጋሚ የሚከሰቱ የሰላም እና የጸጥታ ችግሮችን ተቀናጅቶ ለመከላከል በትብብር መሥራት የሚቻልበትን ሁኔታ መፍጠር ላይ ልዩ ትኩረት መስጠታቸውም ተነግሯል፡፡

በሁለቱም ክልሎች የሚፈጠሩ የጸጥታ ችግሮችን ተከትሎ በንጹሃን ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለዉን ሞትና መፈናቀል በፍጥነት ማስቆም፣ የግጭቱ ጠንሳሾች እና ተዋናዮች ላይ አስፈላጊዉን እርምጃ መዉሰድ ላይ ተኩረት ሰጥተው መወያየታቸውን አብመድ ዘገቧል።

በተከሰቱ ግጭቶች ጉዳት የደረሰባቸዉ ወገኖች ፍትሕ እንዲያገኙ እና ወንጀለኞች ለሕግ እንዲቀረቡ ማድረግ፣ የተፈናቀሉ ወገኖች ወደ ቀያቸው በፍጥነት መመለስና ማቋቋም እንዲሁም በክልሎቹ ዘላቂ ሰላም ከማስፈን አኳያ በትብብር ለመሥራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የሁለቱ ክልሎች አመራሮች ተወያይተዋል።

የሁለቱም ክልሎች ከፍተኛ አመራሮች የተሳተፉበት መድረኩ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር እና በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በጋራ የተመራ መሆኑንም አስታውቋል፡፡

LEAVE A REPLY