– የእነእስክንድር የምርጫ ተሳትፎም ተከለከለ!
ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የእነ ጃዋር መሀመድን ጉዳይ እያየ ያለው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የጸረ ሽብርና የህገ መንግስት ጉዳዮች ወንጀል ችሎት፣ ዐቃቤ ህግ ያቀረበው “ለምስክሮቼ ደህንነት ሲባል ከመጋረጃ በስተጀርባ እና በዝግ ችሎት ምስክሮቼን ላሰማ” ጥያቄን ሳይቀበለው መቅረቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡
አቶ ጃዋር መሀመድን ጨምሮ ሁሉም ተጠርጣሪዎች በተገኙበት ጉዳያቸውን ለማየት ዛሬ የተሰየመው ችሎቱ፣ ዐቃቤ ሕግ ባለፈው ቀጠሮ “በምስክር ጥበቃ አዋጅ 699/2003 አንቀጽ 4 /1 ሸ እና ቀ መሰረት ለ146 ምስክሮች ጥበቃ ተደርጓል ብሎ ከመጥቀስ በዘለለ ምስክሮች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት በማስረጃ ያላስደገፈ በመሆኑ በቂ ምክንያት ሆኖ አላገኘሁትም” በማለት ነው ምስክሮቹ በግልጽ ችሎት ምስክርነታቸውን እንዲሰጡ ብይን የሰጠው።
ተከሳሾቹ ባለፈው ቀጠሮ “የመከላከል መብታችንን የሚገድብ እና የዐቃቤ ህግ አቤቱታ ታማኝነት የለውም” በማለት አቤቱታው ውድቅ እንዲደረግና “የምስክሮች ዝርዝር ይገለጽልን” ብለው አቤቱታን አቅርበው የነበረ ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱ ግን ለምስክሮች ደህንነትና መብት ጥበቃ ሲባል የምስክሮች ማንነት እንዳይገለጽ ሲል ጥያቄውን ውድቅ አድርጎ “የምስክሮች ዝርዝር ሳይገለጽ ምስክርነታቸው በግልጽ ችሎት እንዲሰማ” ብይን ሰጥቷል።
በሌላ በኩል፣ የኦነግ ስራ አስፈፃሚ አባል የሆኑት አቶ አብዲ ረጋሳ ጉዳይ በተከላካይ ምስክሮች አለመገኘት ተለዋጭ ቀጠሮ የተሰጠበት ሲሆን፣ ከተከሰሱበት ሶስት ክሶች 1 ውድቅ ሲደረግ ሌላኛውን እንዲከላከሉ በመባሉ ጉዳያቸው በፍርድ ቤት መታየት መቀጠሉ ተመልክቷል።
ትላንት የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍ/ቤት ወንጀል ችሎት ቀርበው የመከላከያ ምስክሮችን ለማሰማት የተያዘው ቀጠሮ ምስክሮች ባለመገኘታቸው ተለዋጭ ቀጠሮ የተሰጠባቸው የአቶ አቶ አብዲ ጠበቃ ቱሊ ባይሳ እንዳሉት፣ ከመከላከያ ምስክሮቹ አንዱ የሆኑትና በእስር ላይ የሚገኙት ኮሎኔል ገመቹ አያና ያልቀረቡት የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት “ከኦሮሚያ ጠ/ፍርድ ቤት በፃፈው ደብዳቤ የደረሰን ትዕዛዝ የተፈረመው በዳኛ ሳይሆን በህግ ኦፊሰር ነው ስለዚህ በዚህ ትዕዛዝ አናቀርብም” በማለቱ፣ ሌላው ምስክር የኦነግ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ ያልቀረቡትም የፍርድ ቤት የአቶ አብዲ ቤተሰቦች የፍርድ ቤቱን መጥሪያ ይዘው ወደ አቶ ዳውድ ቤት ቢሄዱም የመንግስት ፀጥታ ኃይሎች አካባቢውን በመቆጣጠራቸው ወደ ቤት ገብተው መጥሪያ መስጠት እንዳይችሉ በመከልከላቸው እንደሆነ ለመረዳት ተችሏል።
አቶ አብዲ ረጋሳ ከታሰሩ ከ1 ዓመት በላይ የሆናቸው ሲሆን በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ፍርድ ቤቶች ሲቀርቡ መቆየታቸውንና 3 ጊዜ የዋስትና መብት ተፈቅዶላቸው መዝገባቸውም ተዘግቶ እንደነበር ጠበቃቸው ተናግረዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የባልደራስ ፓርቲ ሊቀመንበር እስክንድር ነጋን ጨምሮ አራት በእስር ላይ የሚገኙ አመራሮች በመጪው ምርጫ በዕጩነት መወዳደር የለባቸውም ሲል ምርጫ ቦርድ የሰጠውን ውሳኔ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት 1ኛ የምርጫ ጉዳዮች ችሎት ዛሬ አጸና።
ፍርድ ቤቱ የባልደራስ ፓርቲ ሊቀመንበር እስክንድር ነጋን ጨምሮ አራት በእስር ላይ የሚገኙ አመራሮች በመጪው ምርጫ በዕጩነት መወዳደር የለባቸውም ሲል ምርጫ ቦርድ የሰጠውን ውሳኔ አጸና።
ከዚህ ቀደም የባልደራስ ፓርቲ ሊቀመንበሩን እስክንድር ነጋን፤ ስንታየሁ ቸኮል እና ቀለብ ስዩምን ጨምሮ በእስር ላይ የሚገኙ አራት አመራሮች “ለመጪው ምርጫ በዕጩነት ይቅረቡልኝ” ሲል ፓርቲው ያቀረበው ጥያቄ በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በኩል ተቀባይነት ሳይገኝ መቅረቱና ፓርቲው ፓርቲው አቤቱታውን ወደ ፍ/ቤት መውሰዱ፣ አቤቱታው የቀረበለት የከፍተኛ ፍርድ ቤት የ1ኛ የምርጫ ጉዳዮች ችሎትም ምርጫ ቦርድ ምላሽ እንዲሰጥበት ማድረጉ የሚታወስ ሲሆን፣ የፓርቲውን ይግባኝ እና እና የምርጫ ቦርዱን ምላሽ አግባብነት አለው ወይስ የለውም የሚለውን መከራከሪያ ነጥብ የመረመረው የዛሬው ችሎች በአብላጫ ድምጽ “የምርጫ ቦርዱ ውሳኔ አግባብነት አለው” ሲል አጽንቶታል።