ፓርቲዎች ከነገ ጀምሮ የሚዲያ ቅስቀሳ ይጀምራሉ! ኢዜማ የቃል ኪዳን ሰነድ ማዘጋጀቱን...

ፓርቲዎች ከነገ ጀምሮ የሚዲያ ቅስቀሳ ይጀምራሉ! ኢዜማ የቃል ኪዳን ሰነድ ማዘጋጀቱን አስታወቀ!

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– የፖለቲካ ፓርቲዎች ነፃ የአየር ሰዓት እና የጋዜጣ አምድ ዕጣ ድልድል በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና ብሮድካስት ባለሥልጣን በተዘጋጀ የጋራ መድረክ በዛሬው እለት የተካሄደ ሲሆን ፓርቲዎቹ ከነገ መጋቢት 30 እስከ ግንቦት 23/2013 ዓ.ም ነፃ የምርጫ ቅስቀሳዎችን በብዙኃን መገናኛዎች ማድረግ እንደሚችሉ ተገልጿል።

ለምርጫ ቅስቀሳው በሬዲዮ 620፣ በቴሌቪዥን 425 ሰዓት እንዲሁም በጋዜጣ 615 አምድ መመደቡ በተገለፀበት የዛሬው መርሃ ግብር፣ ድልድሉ ፓርቲዎች ለፌደራል እና ለክልል ምክር ቤቶች ባቀረቡት እጩ ብዛት እንዲሁም ባስመዘገቡት የሴቶች እና የአካል ጉዳተኛ እጩዎች ብዛት የተሰላ መሆኑና ድልድሉ በ60 የመንግስትና የግል ሚዲያዎች ላይ የተደረገ መሆኑ ተመልክቷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የኢትዮጵያ ዜጐች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በአዲስ አበባ ደረጃ ለሚካሄደው ምርጫ 138 እጩዎችን ማቅረቡንና የምርጫ ቃል ኪዳን ሰነድ ማዘጋጀቱን አስታወቀ።

የኢዜማ መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በአዲስ አበባ ደረጃ የተዘጋጀውን የምርጫ የቃል ኪዳን ሰነድ ዛሬ ይፋ በተደረገበት ወቅት እንደገለጹት፣ ኢዜማ በእያንዳንዱ ወረዳ የህብረተሰቡን 10 መሰረታዊ ችግሮች በመለየት ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ፕሮግራም አዘጋጅቷል።
ኢዜማ ቢመረጥ በህዝቡ ዘንድ የሚስተዋሉትን መሰረታዊ ችግሮች ለመቅረፍ እንደሚሰራም አስታውቀዋል።

በዚሁ ኘሮግራም ላይ ኢዜማ በአዲስ አበባ ከተማ የሚስተዋሉ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮችን ሊፈታ የሚችል የምርጫ ማኒፊስቶ ማዘጋጀቱን የገለጹት ደግሞ ፓርቲውን በመወከል ለአዲስ አበባ ምክር ቤት በእጩነት የቀረቡት አቶ ክቡር ገና ሲሆኑ፣ በከተማዋ ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ የመጣውን የኑሮ ውድነት፣ የመኖሮያ ቤት ችግር፣ የስራ አጥነት ቁጥር መበራከትና ሌሎች የከተማዋን ችግሮችን ሊፈታ የሚችል የቃል ኪዳን ሰነድ ማዘጀታቸውን ገልጸዋል።

LEAVE A REPLY