– ግብፅና ሱዳን የጦርነት አዝማሚያ እያሳዩ ነው!
– የህዳሴው ግድብ ጉዳይ አቅጣጫውን እንዳይስት ተሰግቷል!
ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን እስከዛሬ ያደረጓቸውን ድርድሮች ያለፉ ሂደቶች በመገምገም ድርድሩ የሚቀጥልበትን ሂደት ለመወሰን፣ ኪንሻሳ ላይ ከቀናት በፊት የተጀመረው ስብሰባ በግብፅና ሱዳን ያልተጠበቀ ጥያቄ ለጊዜው መቋረጡ ይታወቃል። ጉዳዩን በሚመለከትም የኢፌዲሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተርር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ መግለጫ ሰጥተዋል።
በስብሰባው መክፈቻ ንግግር ያደረጉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት የድርድር ሂደት እንዲቀጥል እና በውጤት እንዲጠናቀቅ የበኩሏን ጥረት እንደምታደርግ ገለፀዋል። አባይ የድንበር ተሻጋሪ ሀብት እንደመሆኑ የተፋሰሱ ሀገራት ፍትሐዊና ምክንያታዊ መርህን መሰረት ባደረገ አኳኋን የመጠቀም መብት እንዳላቸው እንዲሁም በተፋሰሱ ላይ የሰፈነው የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ብቸኛ ተጠቃሚነትን የማስቀጠል ፍላጎት መቀየር ያለበትና በትብብር እና መግባባት ሊወሰን እንደሚገባ የውጭ ጉዳይ ሚ/ር መግለጫ አመልከቷል።
ይሁንና የግብጽ እና ሱዳን ታዛቢዎች ከአፍሪካ ህብረት እኩል ተሳትፎ የማድረግ ሚና ሊሰጣቸው ይገባል በሚል ያቀረቡት ሀሳብ ተቀባይነት እንዳላገኘ፣ በስብሰባው ሶስቱም ታዛቢዎች ማለትም ደቡብ አፍሪካ፣ አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት በታዛቢነት እንዲቀጥሉ ስምምነት ቢደረስም በአንፃሩ፣ ግብጽ እና ሱዳን በሁለቱ ቀናት ውይይት ያልተነሱ ጉዳዮችን ካልተካተቱ በሚል ረቂቁን አለመቀበላቸውን አስታውቋል።
“የሁለቱ ሀገሮች አካሄድ የአፍሪካ ህብረትን ሚና የሚያሳንስ መሆኑን” የገለፀው መግለጫው፣ ጉዳዩን ከህብረቱ የሚያወጣ ስልት በመከተል እንዲሁም ምክክር የተደረገባቸውን ጉዳዮች የያዘ መግለጫ አንቀበልም በማለት ድርድሩ አዎንታዊ ውጤት እንዳይኖረው እንቅፋት መሆናቸው ገልጿል።
“የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዓመት የውሃ ሙሌት በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ ይከናወናል፤ በሁለቱ ሀገሮች ስምምነት ሳይደረስ ግድቡ መሞላት የለበትም በሚል የሚቀርብ አቋም የሕግ መሰረት የሌለው እንዲሁም የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ሀብቷን የመጠቀም መብት የሚጋፋ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም። ኢትዮጵያ ፍትሐዊ እና ምክንያታዊ የሆነ የአሁን እና የወደፊት በአባይ ውኃ የመጠቀም መብቷን የሚያቅብ ማናቸውም ዓይነት ስምምነት አትፈርምም” ሲልም አስታውቋል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ፣ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጅ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ መዲና ኪንሻሳ የተደረገውን የሶስቱ ሀገራት የውጭ ጉዳይና የውሃ ሚኒስትሮች ውይይት በሚመለከት በሰጡት መግለጫ፣ ካይሮ እና ካርቱም ድርድሩን የማጓተት ስትራቴጂን በመከተላቸው ሰፊ ጊዜ መጥፋቱን አመልክተው “ግብፅ እና ሱዳን የአፍሪካ ህብረት የተሰጠውን ሃላፊነት የሚያንኳስስ ሙከራ ማድረጋቸው ተቀባይነት የለውም” ብለዋል።
ደቡብ አፍሪካ ከታዛቢነት እንድትወጣ ሀሳብ መቅረቡንና ይህም “የአፍሪካ ህብረትን ክብር የማይመጥን ነው” ያሉት ሚኒስትሩ፣ የድርድሩን ቅርጽ የመለወጥ እና ከይዘት ይልቅ ሂደት ላይ ማተኮር በኪንሻሳው ስብሰባ ላይ መታየቱን፣ ኢትዮጵያ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ በኩል ድርድሩ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ የአባይን ውሃ ምክንያታዊ እና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ የመጠቀም ሉዓላዊ መብቷን ማስረዳቷን፣ ኢትዮጵያ ከትብብር ይልቅ የአንድ ወገን ተጠቃሚነትን ለሚያረጋግጥ ሃሳብ ምንም አይነት ቦታ እንደሌላት ማሳወቃቸውንና ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት በተያዘለት ጊዜ እንደሚካሄድ አስታውቀዋል።
በግብፅና ሱዳን በኩል “ግድቡን እናጠቃለን” በሚል ተደጋግመው የሚሰሙ ዛቻዎች እውን ይሆናሉ የሚል ግምት እንደሌላቸውም ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል፣ በሱዳን አብዬ ግዛት የሚገኘው የኢትዮጵያ ሰላም አስካባሪ ኃይል ከቦታው ለቆ እንዲወጣ ሱዳን ለተመድ ጥያቄ ማቅረቧን ትናንት በይፋ አስታውቃለች፡፡
ሱዳን ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰቸው በኪንሻሳ የተካሄደው የግድብ የሶስትዮሽ ድርድር ያለስምምነት መጠናቀቁን ተከትሎ ሲሆን፣ የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሬም አልሳዲግ አልመሀዲም “ኢትዮጵያ በሱዳን ላይ ብዙ ፍላጎት አላት፤ ሱዳን ጥቅሟን ለማስከበር ብዙ አማራጮችን ትጠቀማለች። ኢትዮጵያ ያለችበትን የውስጥ ችግር ሱዳን ተረድታ ለረጅም ጊዜ ታግሳለች። በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞችን ተቀብለና፤ ከእንግዲህ ግን ይህ ያበቃል። በቀጥታ ብሔራዊ ጥቅማችንን ማስከበር ላይ እናተኩራለን። በመሆኑም በአብዬ ግዛት በተሰማራው የኢትዮጵያ ሰራዊት ላይ እምነት ስለሌለንም ጦሩ በፍጥነት አብዬን ለቆ እንዲወጣ እንፈልጋለን” የሚል መግለጫ ሰጥተዋል።
ከ4 ሺህ በላይ ቁጥር ያለው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል፣ በተባበሩት መንግስታት ስር በመሆን በሱዳን እና በደቡብ ሱዳን መካከል በምትገኘውና ሁለቱ ሀገራት “የይገባኛል ጥያቄ በሚያቀርቡባት” አብዬ ግዛት ከፈረንጆቹ 2011 ጀምሮ ሰላም ለማስከበር ሰፍሮ ቆይቷል፡፡
ይሁንና ይህን የሱዳን መንግስት የጦርነት አዝማሚያ የታዘቡት የሱዳን የቀድሞ ውሀና መስኖ ሚኒስትር ዶ/ር ኡስማን አቶክ “የዉሀ ጉዳይን በጦርነት ለመፍታት ማሰብ የዋህነት ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
“የውሃ ችግር የሚፈታው በውይይት ነው” ዶ/ር ኡስማን ግብፅና ሱዳን በቅርቡ ያደረጉትን የጋራ ወታደራዊ ልምምድን በሚመለከትም “ወታደራዊ ልምምዱ ከልምምድ ያለፈ ሆኖ አይታየኝም። ምክንያቱም ሁሉንም ለሚፈልጉት ትርፍ አያበቃም። በወታደራዊ ሀይል ተጠቅሞ መፍትሔ የሚያስብ ካለ እሱ በሌላ ፕላኔት የኖረ ነው። ለሁሉም የሚጠቅመው እና የሚያስፈልገው በሰላም ተነጋግሮ በመግባባት አዲስ ስምምነት ለማድረግ መስራት ነው” ብለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ግብፅና ሱዳን በጋራ ሆነው ኢትዮጵያ ላይ ጥቃት ሊሰነዝሩ ይችላሉ በሚል በርካታ ኢትዮጵያዊያን ስጋታቸውን በተለያየ መንገድ ሲገልፁና ሀገሪቱ የሚቃጣባትን ጥቃት ለመመከት ያላትን ዝግጁነት ሲጠይቁ የሚደመጥ ሲሆን፣ የመከላከያ አቬዬሽን በቅርቡ ይፋ ባደረገው መረጃ የህዳሴ ግድቡ የአየር ቀጣና ከአየር በረራ ነፃ መደረጉ ተመልክቷል።
ይህን የአየር ክልል ጥሶ ለማለፍ የሚሞክር በራሪ አካል በአየር መቃወሚያ ቴክኖሎጂዎቻችን እንደሚመታና ዘመናዊ የአየር መቃወሚያ ተገጥሞ ሁሌም ለ24 ሰዓታት በንቃት እየተጠበቀ መሆኑን የገለፀው የመከላከያ አቬዬሽን፣ መሳሪያው እስከ 400 ኪ.ሜትር ርቀት ቅኝት የሚያደርግና በዚህ ርቀት የሚመጣ በራሪ አካልን የማምከን አቅም እንዳለውም ጠቁሟል።
አገራችን Pantsir የተባለውን አየር መቃወሚያ ከራሺያ መረከቧን military watch magazine እና ስፑትኒክ የተባለው የራሺያው አምራች ድርጅት ራሱ በይፋ አስታውቀዋል። የእስራኤሉን ስፓይደር የተባለ ሚሳኤል በህዳሴው ግድብ አካባቢ ተከላውን የተለያዩ ወታደራዊ ኢንተለጀንስ ተቋማትን ዋቢ አድርገው በርከት ያሉ ሚዲያዎች ዘግበዋል።
ራሺያ ሰራሹ “Pantsir” አውሮፕላኖችን፣ የጦር ጀቶችን፣ ሄሌኮፕተሮችን፣ ከጦር ጀቶች ላይ የሚተኮሱ ቦምቦችን፣ ሚሳኤሎችን እና ሰው አልባ አውሮፕላኖችን በፍጥነት ማውደም የሚችል የዘመነ የአየር መቃወሚያ ሲስተም መሆኑ ይታወቃል።