በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች የእሳት አደጋ ደረሰ! በከተማዋ የነዳጅ እጥረት ድጋሚ ተከስቷል!

በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች የእሳት አደጋ ደረሰ! በከተማዋ የነዳጅ እጥረት ድጋሚ ተከስቷል!

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– በአዲስ አበባ ከተማ ትናንት ማምሻውን ብቻ በደረሰው የእሳት አደጋ ከ7 ሚሊየን 550 ሺህ ብር በላይ ግምት ያለው ንብረት መውደሙ ተገልጿል

በትናንትናው ምሽት በከተማዋ አራት አካባቢዎች የእሳት አደጋ መከሰቱን የገለፀው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር እሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን፣
የእሳት አደጋዎቹ የተከሰቱት በአቃቂ ቃሊቲ፣ ኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ከተሞች እንዲሁም በየካ ክፍለ ከተማ በሁለት የተለያዩ አካባቢዎች መሆኑን አመልክቷል።

“አቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ ወረዳ 8 “መልካ ሸኔ” ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ከምሽቱ 12 ሰዓት ከ50 ገደማ በከብቶች በረትና በ7 አባወራ ቤቶች ላይ ቃጠሎ ደርሶ ውድመት መድረሱንና በአደጋው 9 ላሞችና ሁለት ጥጆች መሞታቸውን፣ በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 ወይራ ሰፈር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሌሊት 7 ሰዓት ላይ በመስጂድ ቅጥር ግቢ በሚገኝ መጋዘን ላይ የእሳት አደጋ መከሰቱ ታውቋል።

በተያያዘ በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ልዩ ቦታው “ስኩል ኦፍ ቱሞሮው” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሌሊት 6 ሰዓት ገደማ የመኖሪያ ቤት መቃጠሉን፣ በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሁለት “መለስ ፋውንዴሽን” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከሌሊቱ 4 ሰዓት ገደማ በአንድ ማተሚያ ቤት በደረሰው የእሳት አደጋ ጉዳት መድረሱን ያስታወቀው ኮሚሽኑ፣ የአደጋዎቹ መንስኤ በመጣራት ላይ መሆኑንም አመልክቷል።

በአገራችን የተለያዩ አካባቢዎች ባልተለመደ መልኩ እእየተከሰተ ያለውን የእሳት ቃጠሎ አደጋ በሚመለከት ሰፊ ዘገባ ማቅረባችን ይታወሳል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በአዲስ አበባ ከተማ የነዳጅ እጥረት ማጋጠሙ እየተነገረ ሲሆን፣ አቅርቦቱን በሚሰጡ ማደያ ጣቢያዎች የሚታየው ረጃጅም የተሽከርካሪዎች ሰልፍም እጥረቱ ለመከሰቱ አይነተኛ ማስረጃ ሆኖ እየተጠቀሰ ይገኛል።

እስካሁን ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት በኩል የተሰጠ ይፋዊ መግለጫ ባይኖርም አብዛኞቹ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪዎች በመቆማቸው ተጠቃሚው ህብረተሰብ ሲንገላታ መዋሉን ለማወቅ ተችሏል።

LEAVE A REPLY