ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በአዲስ አበባ ከተማ የሚኖሩ አንዳንድ የውጭ ሀገር ዜግነት ያላቸው ግለሰቦች ሀብትና ንብረት ያላቸውን ኢትዮጵያዊያንን ማንነት በጥናት በመለየትና ግነኙነት በመፍጠር ከፍተኛ የሆነ የማጭበርበር ወንጀል እየፈፀሙ መሆኑን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።
የውጭ ሀገር ዜጎቹ ኢንቨስተር ነን በሚል ከፍተኛ የማጭበርበር ወንጀል በመፈፀም በዜጎች ላይ ጉዳት እያደረሱ መሆኑን የገለፀው የኮሚሽኑ ወንጀል ኢንተለጀንስ እንዳረጋገጠው፣ እነዚህ የውጭ ሀገር ዜጎች ወደ ሀገራችን ለኢንቨስትመንት የመጡ በማስመሰል፣ አብረዋቸው የሚሰሩ ኢትዮጵያዊያንን እንደሚፈልጉ በማግባባት እንደሚጠቀሙ ታወቋል።
ለስራ ማስኬጃም ከ300 ሚሊየን ዶላር በላይ እንዳላቸው በመግለጽ፤ ኢትዮጵያዊያንን ካገኙ አብሮ ለመስራት ዝግጁ እንደሆኑ በማስመሰል የሚያጭበረብሩ ሲሆን፣ የኛ ዜጎች አብረዋቸው ቢሰሩ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ በማሳመን እና ከዚህ በተጨማሪም ዶላር የማባዛት ችሎታ እንዳላቸው በመግለፅ በተግባር አባዝቶ ለማሳየት መጀመሪያ የያዙትን ዶላር ሌላ ቦታ በፖስታ በመደበቅና ይባዛበታል ያሉትን ወረቀት ኬሚካል ውስጥ በመንከር ከዚያም የተነከረውን ወረቀት አውጥተው እንዲደርቅ በማድረግ በሌላ ፖስታ ውስጥ ያስቀመጡትን ትክክለኛ ዶላር በእጥፍ እንዳባዙት በማስመሰል ለሰዎቹ ያሳዩና ይበልጥ አመኔታን ለማግኘት ተባዛ ያሉትን ዶላር ባንክ ቤት ይዘው እንዲሄዱና ትክክለኛነቱን አረጋግጠው እንዲመጡ ካደረጉ በኋላ አሁን የተባዛውን ዶላር ትክክለኛ መሆኑን ስላረጋገጥን እስከ አንድ ሚሊየን ዶላር ይዛችሁ ኑና እናባዛ በማለት ወደ ማጭበርበር ተግባር እንደሚያስገቡም የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ኢንተለጀንስ አሳውቋል፡፡
የኢትዮጵያን የብር ኖት በእጥፍ ማባዛት እንደሚችሉ በማስረዳትና ሃብታም እንደሚሆኑ በማሳመንም ዜጎቻችን ያላቸውን ገንዘብ ይዘውላቸው ሲሄዱ ግማሾቹ ከነገንዘቡ ታፍነው ገሚሶቹ ደግሞ እራሳቸውን ስተው እንደተገኙና ገንዘባቸውንም እንደተቀሙ ማረጋገጥ መቻሉን ያሳወቀው የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ኢንተለጀንስ፣ የዚህ የማጭበርበር ወንጀል ሰለባዎችም ቤተሰቦቻቸው መበተኑን፣ ለድህነትና ለጤና መታወክ እንደተዳረጉ ማረጋገጡን ገልፆ “ህብረተሰቡ ሁኔታውን ተገንዝቦ የማይገባ ጥቅም አገኛለሁ ብሎ ለእንደነዚህ ዓይነት አጭበርባሪዎች ሲሳይ እንዳይሆን እንዲሁም እራሱንና ቤተሰቡን እንዲጠብቅ” ሲል አሳስቧል።
በተያያዘ፣ በአዲስ አበባ ከተማ በጥናት ላይ ተመርኩዞ ባደረገው ቁጥጥር ተደራጅተው ከባድ የዘረፋ ወንጀል ሲፈጽሙ የነበሩ 34 ተጠርጠሪዎች እና 12 ተሸከርካሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
የተጠርጣሪዎቹ የወንጀል አፈፃፀም አደገኛ መሆኑን የገለፁት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀልና ትራፊክ አደጋ ምርመራ ም/ኮሚሽነር ሃሰን ነጋሽ፣ ሃሰተኛ የቀበሌ መታወቂያ የሚያዘጋጁ፣ የጥበቃ ሰራተኛ መስለው ለሚቀጠሩ ወንጀል ፈፃሚዎች ሃሰተኛ ተያዥ የሚያፈላልጉና በሚዘረፈው ተቋም ላይ የጥበቃ ሰራተኛ ሆኖ እንዲቀጠር አድርገው ሌሎች የጥበቃ ሰራተኞችን በተለያዩ አደገኛ መድሃኒቶች በማደንዘዝ ለዘረፋ ምቹ ሁኔታን በሚፈጥሩ ግለሰቦች የተደራጀ ቡድን እንደነበረም አብራርተዋል፡፡
በተጨማሪ የተዘረፈውን ንብረት ጭኖ የሚወስድ፣ ደልሎ የሚያሻሽጥ፣ ለተሰረቁ ተሸከርካሪዎች የሻንሲ ቁጥራቸውን የሚቀይር እና ንብረቶቹን የሚገዛ ቡድን ያለበት አደገኛ ስብስብ እንደነበርም ኃላፊው ገልፀዋል፡፡