ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– “በሀገሪቱ የምርጫ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከናወነው ነው” የተባለለት የድምፅ መስጫ ወረቀት የህትመት ቅደም ተከተል ዕጣ የማውጣት ስነ- ስርዓት ዛሬ ተካሂዷል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ የሚሳተፉ ተፎካካሪ ፖርቲዎች በድምፅ መስጫ ወረቀት ላይ የሚኖራቸውን ቅደም ተከተል ለመወሰን ያካሄደው ዕጣ የማውጣት ስነ- ስርዓት፣ ለተከታታይ 4 ቀናት በሁሉም የምርጫ ክልሎች ያካሄደው የዕጣ ማውጣት ስነ-ስርዓት ማጠቃለያ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን፣ በዛሬው የማጠቃለያ ፕሮግራሙም የሁሉም የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች መገኘታቸው ተመልክቷል።
በዕጣ ማውጣት ስነስርዓት ላይ የተገኙ የፖለቲካ ፖርቲ ተወካዮች “ይህ አይነቱ የድምፅ መስጫ ወረቀት የህትመት ቅደም ተከተል ዕጣ የማውጣት ስነ-ስርዓት ለምርጫው ዲሞክራሲያዊና ግልጽነት መስፈን፣ የሰላማዊ ሂደቱም አንዱ ማሳያ እንደሆነ” የገለፁ ሲሆን፤ የብልፅግና ፓርቲን በመወከል በዕጣ ማውጣት ስነስርዓቱ ላይ የተሳተፉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤም፣ ምርጫው ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ግልፅነት የሰፈነበትና አሳታፊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የተሰጣቸውን ሀላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በዚሁ ስነ ስርዓት “ምርጫ የምናካሂደው ለሀገር ሉዓላዊነትና ለዜግነት ክብር በመሆኑ ሁሉም ተፎካካሪዎች የምርጫ ህጉን አክብረው መሳተፍ ይገባል” ሲሉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ መናገራቸውንም ለመረዳት ተችሏል።